ምሳሌ 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በከንፈሩ ከሚወሳልት አላዋቂ ይልቅ፥ ያለ ነውር የሚሄድ ድሃ ይሻላል። 2 ነፍስ ዕውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ እግሩንም የሚያፈጥን ከመንገድ ይስታል። 3 የሰው ስንፍናው መንገዱን ያጣምምበታል፥ በልቡም እግዚአብሔርን ገፋኢ ያደርገዋል። 4 ባለጠጋ ብዙ ወዳጆችን ይጨምራል፤ ድሃ ግን ያን ያለውን ያጣል። 5 ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፥ በግፍዕ የሚከስም አያመልጥም። 6 ብዙ ሰዎች በነገሥታት ፊት ያገለግላሉ፥ ነገር ግን የሰው ጽድቁና ሀብቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ናቸው፤ ክፉ ሁሉም የሰው መዘባበቻ ይሆናል። 7 ድሃ ወንድሙንም የሚጠላ ሰው ሁሉ፥ ከወንድምነቱ የራቀ ነው። በጎ ዕውቀትም ወደሚያውቋት ትቀርባለች። ብልህ ሰውም ያገኛታል። ብዙ ክፋትን የሚሠራ ክፋትን ይፈጽማል፥ ስቅጥጥ የሚያደርግ ነገርን የሚናገርም አይድንም። 8 ጥበብን የሚያገኝ ራሱን ይወድዳል፥ ማስተዋልንም የሚጠብቅ መልካም ነገርን ያገኛል። 9 ሐሰተኛ ምስክር ከቅጣት አይድንም፤ ክፋትን የሚያቀጣጥላትም ይጠፋባታል። 10 ለአላዋቂ ቅምጥልነት አይገባውም፥ አገልጋይም ከስድብ ጋር ቢገዛ ይበረታል። 11 ይቅር ባይ ሰው ይታገሣል፥ መመካቱም ኀጢአተኞችን ይቃወማቸዋል፥ 12 የንጉሥ ቍጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፥ ሞገሱም በመስክ ላይ እንዳለ ጠል ነው። 13 አላዋቂ ልጅ ለአባቱ ኀፍረት ነው፥ ከዐስበ ደነስ ጋር የሚቀርብ ስእለትም ንጹሕ አይደለም። 14 አባቶች ለልጆቻቸው ቤትንና ሀብትን ያወርሳሉ፤ ሚስት ግን በእግዚአብሔር ከባልዋ ጋር አንድ ትሆናለች። 15 ችግረኛን ሰው ሽብር ይይዘዋል፥ የማይሠራ ሰውም ይራባል። 16 ትእዛዛትን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ መንገዶቹን የሚያቃልል ግን ይጠፋል። 17 ለድሃ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ እንደ ስጦታውም መልሶ ይከፍለዋል። 18 ለተስፋ ይሆንህ ዘንድ ልጅህን ግረፍ፥ ለመሳደብ ግን እጅህን አታንሣ፥ 19 ዐሳበ ክፉ ሰው ብዙ ያጠፋል፤ ጽኑ ደፋር ቢሆን ግን ነፍሱን ይጨምራል። 20 ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ። 21 በሰው ልብ ብዙ ዐሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘለዓለም ይኖራል። 22 ምጽዋት ለሰው ፍሬ ነው፤ ከሐሰተኛ ባለጠጋም እውነተኛ ድሃ ይሻላል። 23 እግዚአብሔርን መፍራት የሰው ሕይወት ነው፤ የማይፈራው ግን ዕውቀት በሌለበት ቦታ ውስጥ ይኖራል። 24 ታካች ሰው እጁን በብብቱ ይሸሽጋል፥ ወደ አፉ ስንኳ አይመልሳትም። 25 ፌዘኛን ብትገርፈው አላዋቂው ብልሃተኛ ይሆናል፤ አስተዋይን ሰው ብትገሥጸው ግን ዕውቀትን ያገኛል። 26 አባቱን የሚያዋርድ እናቱንም የሚያሳድድ፥ አሳፋሪና ጐስቋላ ልጅ ይሆናል። 27 የአባቱን ትምህርት ከመጠበቅ የሚከለከል ልጅ፥ ክፉ ቃልን ይማራል። 28 ለአላዋቂ ልጅ የሚዋስ ፍርድን ያስነቅፋል፥ የኃጥኣንም አፍ ክፉ ቅጣትን ይውጣል። 29 ለክፉዎች ሰዎች መቅሠፍት ተዘጋጅቶላቸዋል፥ ለሰነፎችም እንደዚሁ ቅጣት። |