ኤርምያስ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ባዕድ አምልኮትና እውነተኛ አምልኮ 1 እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ! እግዚአብሔር በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የአሕዛብን መንገድ አትማሩ፤ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፤ አሕዛብ ከእነርሱ የተነሣ ይፈራሉና። 3 የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፥ ከዱር በመጥረቢያ እንደሚቈረጥ፥ በሠራተኛም እጅ እንደሚሠራ እንጨት ነው። 4 በብርና በወርቅ ይለብጡታል፤ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል። 5 እንደ ተቀረጸ ብር ናቸው፤ እነርሱም አይናገሩም፤ መራመድም አይቻላቸውምና ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራትም አይቻላቸውምና፥ ደግሞም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው።” 6 አቤቱ! እንደ አንተ ያለ የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኀይል ታላቅ ነው። 7 የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ! በአሕዛብ ጥበበኞች ሁሉ መካከል፥ በመንግሥታቸውም ሁሉ እንደ አንተ ያለ ስለሌለ፥ ለአንተ ክብር ይገባልና አንተን የማይፈራ ማን ነው? 8 በአንድ ጊዜ ሰንፈዋል፥ ደንቍረውማል፤ ጣዖታት የሚያስተምሩት የእንጨት ነገር ብቻ ነው። 9 የሠራተኛና የአንጥረኛ እጅ ሥራ የሆነ ከተርሴስ ጥፍጥፍ ብር፥ ከአፌዝም ወርቅ ይመጣል፤ ልብሳቸውም ሰማያዊና ቀይ ግምጃ ነው፤ ሁሉም የብልሃተኞች ሥራ ናቸው። 10 እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም። 11 እናንተም፦ ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ፥ ከሰማይም በታች ፈጽመው ይጥፉ ትሉአቸዋላችሁ። 12 ምድርን በኀይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ ያጸና፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። 13 በላይ በሰማይ ውኆችን ይሰበስባል፤ ከምድርም ዳርቻ ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናብም መብረቅን ያደርጋል፤ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። 14 ሰው ሁሉ ዕውቀት አጥቶ ሰንፎአል፤ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የለውምና። 15 አገጣጥመው የሚሠሩት ሥራ ከንቱ ነው፤ በተጐበኙ ጊዜም ይጠፋሉ። 16 የያዕቆብ ዕድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ ሁሉን የፈጠረ ነውና እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። ስለሚመጣው ስደት 17 በምሽግ ውስጥ የተቀመጥሽ ሆይ! ኀይልሽን ከውጭ ሰብስቢ፤ 18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ በምድሪቱ የሚኖሩትን በመከራ አሰናክላቸዋለሁ፤ መቅሠፍትሽም እንዲያገኛቸው አስጨንቃቸዋለሁ። 19 ስለ ስብራቴ ወዮልኝ! ቍስሌም ክፉ ነው፤ እኔ ግን፦ በእውነት የመከራ ቁስሌ ነው፤ እርሱንም መሸከም ይገባኛል አልሁ። 20 ድንኳኔም ተበዘበዘ፤ አውታሬም ሁሉ ተቈረጠ፤ ልጆችና በጎችም የሉም ከእንግዲህ ወዲህ ለድንኳኔም ቦታ የለም ለመንጎችም መሰማሪያ የለም፤ 21 እረኞች አእምሮአቸውን አጥተዋልና፥ እግዚአብሔርንም አልፈለጉትምና፤ ስለዚህም መሰማሪያውን አላወቁም፤ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል። 22 የወሬ ድምፅ ተሰማ፤ እነሆም የይሁዳን ከተሞች ባድማና የሰገኖ ማደሪያ ያደርጋቸው ዘንድ ከሰሜን ምድር ታላቅ መነዋወጥ መጥቶአል። 23 አቤቱ! የሰው መንገድ ከራሱ እንደ አይደለ አውቃለሁ፤ ሰውም አይሄድባትም፤ መንገዱንም ጥርጊያ አላደረገም። 24 አቤቱ! ቅጣን፤ ነገር ግን ፈጽመህ እንዳታጠፋን በፍርድህ ይሁን እንጂ በቍጣህ አይሁን። 25 ያዕቆብን በልተውታልና፥ አጥፍተውትማልና፥ ማደሪያውንም አፍርሰዋልና በማያውቁህ አሕዛብ፥ ስምህንም በማይጠሩ ትውልድ ላይ መዓትህን አፍስስ። |