Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ነህምያ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የጠላት ሴራ መጨናገፍ

1 ሳንበላጥ፥ ጦብያ፥ ዓረባውያን፥ አሞናውያንና አሽዶዳውያን የሚታደሰው የኢየሩሳሌም ቅጥር ከፍ እያለ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም እየተጠገነ እንደሆነ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቆጡ።

2 መጥተው ኢየሩሳሌምን ሊወጉና ሊሸብሩ ሁሉም በአንድነት አሴሩ።

3 ወደ አምላካችን ጸለይን፥ በእነርሱም ምክንያት በሌሊትና በቀን በእነሱ ላይ ጠባቂ አቆምን።

4 ይሁዳም፦ “የተሸካሚዎች ኃይል ደክሟል፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፤ ቅጥሩን መሥራት አንችልም” አለ።

5 ጠላቶቻችንም፦ “በመካከላቸው እስክንገባና እስክንገድላቸው ድረስ፥ ሥራቸውንም እስክናስተጓጉል ድረስ አያውቁም፥ አያዩምም” አሉ።

6 በአጠገባቸው የተቀመጡ አይሁድ መጥተው፦ “ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል” ብለው ዐሥር ጊዜ ነገሩን።

7 እኔም ከቅጥሩ በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን፥ ጦራቸውንና ቀስታቸውን አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኳቸው።

8 አየሁና ተነሣሁ፥ መኳንንቶቹን፥ ሹማምቱንና የተቀረው ሕዝብ፦ “አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስታውሱ፥ ስለ ወንድሞቻችሁ፥ ስለ ወንዶች ልጆቻች፥ ስለ ሴቶች ልጆቻችሁ፥ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ቤቶቻችሁ ተዋጉ።” አልኳቸው።

9 እንዲህም ሆነ፥ ጠላቶቻችን በእኛ ዘንድ እንደታወቀ፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው በሰሙ ጊዜ፥ እኛ ሁላችንም ወደ ቅጥሩ፥ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን።

10 ከዚያን ቀን ጀምሮ እኩሌቶቹ ጎልማሶች ሥራ ሲሠሩ፥ እኩሌቶቹ ጋሻ፥ ጦር፥ ቀስትና ጥሩር ይይዙ ነበር፤ ሹማምቱም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር።

11 ቅጥሩን የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ፥ በአንድ እጃቸው ደግሞ የጦር መሣሪያ ይይዙ ነበር።

12 እያንዳንዱ ግንበኛ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋውም በአጠገቤ ነበረ።

13 መኳንንቱን፥ ሹማምቱንና የቀሩትን ሕዝብ እንዲህ አልኋቸው፦ “ሥራው ብዙና ሰፊ ነው፥ እኛም በቅጥሩ ላይ አንዱ ከሌላው ርቆ ተለያይተናል፤

14 የቀንደ መለከቱን ድምፅ በምትሰሙበት ስፍራ በዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል።”

15 እኛ ሥራውን ሠራን፤ እኩሌቶቹ ደግሞ ጎሕ ሲቀድ ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ ጦር ይይዙ ነበር።

16 እንዲሁም ደግሞ በዚያ ጊዜ ሕዝቡን፦ “በሌሊት ጠባቂዎች፥ በቀንም ሥራ እንዲሰሩልን እያንዳንዱ ከአገልጋዩ ጋር በኢየሩሳሌም ውስጥ ይደር፤” አልኋቸው።

17 እኔ፥ ወንድሞቼ፥ ጎበዛዝቶቼና ከኋላዬ የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር። ወደ ውኃም ስንሄድ እያንዳንዱ መሣሪያውን ይዞ ይሄድ ነበር።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች