Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢዮብ 28 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 “በእውነቱ ብር የሚወጣበት፥ ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ።

2 ብረት ከመሬት ውስጥ ይወሰዳል፥ ከቀለጠ ድንጋይም መዳብ ይወጣል።

3 ለጨለማ ወሰን ይደረጋል፥ የጨለማውንና የሞት ጥላን ድንጋይ እስከ ጫፍ ድረስ ይፈላልጋል።

4 ሰው ከሚኖርበት ርቀው መውረጃ ይቈፍራሉ በመንገድኞችም ተረስተዋል፥ ከሰዎችም ርቀው እየተንጠለጠሉ ይወዛወዛሉ።

5 ምድር እንጀራን ታበቅላለች፥ ከበታቿ ያለው ግን እንደ እሳት ይገለባበጣል።

6 እዚያ ድንጋዮችዋ የሰንፔር መከማቻ ናቸው፥ የወርቅም ድቃቂ ይገኛል።”

7 “መንገድዋን ጭልፊት አያውቀውም፥ የአሞራም ዐይን አላየውም።

8 ኩሩ አውሬዎች አልረገጡአትም፥ ደቦል አንበሳ አላለፈባትም።”

9 “ሰው ወደ ጠንካራ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥ ተራራውንም ከመሠረቱ ይገለብጣል።

10 ከድንጋይ ውስጥ መተላለፍያ ይሠራል፥ ዓይኑም ዕንቁን ሁሉ ታያለች።

11 የወንዞችን መነሻዎች ይፈልጋል፥ የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።”

12 “ነገር ግን ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?

13 ሰው መንገድዋን አያውቅም፥ በሕያዋን አገር አትገኝም።

14 ቀላይ፦ በእኔ ውስጥ የለችም ይላል፥ ባሕርም፦ በእኔ ዘንድ የለችም ይላል።

15 በንጹሕ ወርቅ አትገኝም፥ ዋጋዋም በብር አይተመንም።

16 በኦፊር ወርቅ፥ በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም።

17 ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥ ከጥሩ ወርቅ በተሠራ ዕቃም አትለወጥም።

18 ስለ ዛጐልና ስለ አልማዝ አይነገርም። የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቁ ይልቅ ይበልጣል።

19 የኢትዮጵያ ቶጳዝዩን አይተካከላትም፥ በንጹሕ ወርቅም አትገመትም።”

20 “እንግዲያውስ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?

21 ከሕያዋን ሁሉ ዐይን ተሰውራለች፥ ከሰማይ ወፎችም ተሸሽጋለች።

22 ጥፋትና ሞት፦ ስለ እርሷ በወሬ ሰማን ብለዋል።”

23 “እግዚአብሔር መንገድዋን ያስተውላል፥ እርሱም ስፍራዋን ያውቃል።

24 እርሱም የምድርን ዳርቻ ይመለከታል፥ ከሰማይም በታች ያለውን ሁሉ ያያል።

25 ለነፋስ ሚዛንን ባደረገለት ጊዜ፥ ውኆችንም በስፍር በሰፈረ ጊዜ፥

26 ለዝናብም ሥርዓትን፥ ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን ባደረገ ጊዜ፥

27 በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፥ አዘጋጃትም፥ ደግሞም መረመራት።

28 ሰውንም፦ ‘እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፥ ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው’ አለው።”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች