ኤርምያስ 52:4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር ከወሩም በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም አራት ክንድ ግንብ ሠራ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ስለዚህ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ከተማዪቱንም ከበቧት፤ በዙሪያውም የዐፈር ድልድል ሠሩ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ መጥተው ከበቡአት በዙሪያዋም ለመክበብያ የሚሆን ምሽግ ሠሩባት። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፥ በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በመምጣት በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል አስከበባት፤ ሠራዊቱም በከተማይቱም ዙሪያ ሰፈረ፤ በቅጥሩም ዙሪያ ዐፈር ቈለለ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ መጥተው ከበቡአት በዙሪያዋም ዕርድ አደረገ። |
“የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋን ዘንድ መጥቶአልና ከእኛ ይመለስ ዘንድ፥ ምናልባትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደ ተአምራቱ ሁሉ ያደርግ እንደ ሆነ ስለ እኛ፥ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅ።”
አሕዛብም መጥተው ይህችን ሀገር ያዟት፤ ይህችም ከተማ ከረኃቡና ከጦሩ የተነሣ በወጓት በከለዳውያን ሰዎች እጅ ወደቀች፤ እንደ ተናገርኸውም ሆነ።
የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ፥ ከእጁም ግዛት በታች ያሉ የምድር መንግሥታት ሁሉ፥ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ሁሉ ይወጉ በነበረ ጊዜ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው፦
እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዘጠነኛው ዓመተ መንግሥት በዐሥረኛው ወር የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት።
ከተማዪቱም ተሰበረች፤ ሰልፈኞችም ሁሉ ሸሹ፤ በሁለቱም ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሥ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ከከተማዪቱ ወጡ። ከለዳውያንም በከተማዪቱ ዙሪያ ነበሩ፤ በዓረባም መንገድ ሄዱ።
የቅጥሩን ማፍረሻ ያደርግ ዘንድ፥ አፍንም በጩኸት ይከፍት ዘንድ፥ በውካታም ድምፅን ከፍ ያደርግ ዘንድ፥ የቅጥሩን ማፍረሻ በበሮች ላይ ያደርግ ዘንድ፥ አፈርን ይደለድል ዘንድ፥ ምሽግም ይሠራ ዘንድ የኢየሩሳሌም ምዋርት በቀኝ እጁ ውስጥ ነበረ።
እርሱ በምድረ በዳ ያሉ ሴቶች ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፤ ጠባቂዎችንም በአንቺ ላይ ያስቀምጣል፤ በዙሪያሽም ግንብ ይሠራል፤ የጦር መሣሪያም ይዘው ይከቡሻል፤ በጦራቸውም ይወጉሻል፤
እንዲህም ሆነ፤ በተማረክን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፦ ከተማዪቱ ተያዘች አለኝ።
በተማረክን በሃያ አምስተኛው ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ከወሩ በዐሥረኛው ቀን፥ ከተማዪቱ ከተመታች በኋላ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረ፤ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ።
የቃል ኪዳኔንም በቀል ይበቀልባችሁ ዘንድ ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተማችሁም ትሸሻላችሁ፤ ቸነፈርንም እሰድድባችኋለሁ። በጠላቶቻችሁም እጅ ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ፤
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል፣ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ።
ጠላቶችሽ አንቺን የሚከቡበት ቀን ይመጣል፤ ይከትሙብሻል፤ ያስጨንቁሻልም፤ በአራቱ ማዕዘንም ከብበው ይይዙሻል።