ኢሳይያስ 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ መከበብ 1 ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ ለአርኤል ወዮላት! የዓመቱን አዝመራ ሰብስቡ፤ ከሞዓብ ጋር ትበላላችሁና። 2 አርኤልንም አስጨንቃለሁ፤ ይህችም ኀይል፥ ይህችም ብዕል የእኔ ትሆናለች፥ 3 እንደ ዳዊትም እከብሻለሁ፤ በቅጥርም አጥርሻለሁ፤ አንባም በላይሽ አቆማለሁ። 4 ነገርሽም በምድር ውስጥ ይሰጥማል፤ ቃልሽም ከምድር በታች እንደሚናገር ይሆናል፤ ትደክሚያለሽ፤ ቃልሽም በምድር ውስጥ ዝቅ ይላል። 5 ነገር ግን የኃጥአን ብልጽግና እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጠላቶችሽም ብዛት ነፋስ እንደሚያመጣው ገለባ ይሆናል። 6 ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅ ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል። 7 በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ ኢየሩሳሌምንም የሚወጉ፥ በእርሻዋም ላይ የሚሰበሰቡ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብልጽግና እንደሚያልም ሰው ሕልም ነው። 8 ሰዎች ተርበው ሌሊት በሕልማቸው ይበላሉ፤ ይጠጣሉም፤ በተነሡ ጊዜ ግን ሕልማቸው ከንቱ ነው። የተጠማ ሰውም እንደሚጠጣ ያልማል፤ በነቃም ጊዜ እንደ ተጠማ ነው፤ ነፍሱም በከንቱ ትመኛለች። ደብረ ጽዮንን የሚዋጉ የአሕዛብ ብልጽግናም እንደዚሁ ነው። 9 ደከሙ፤ ደነገጡም፤ ሰከሩም፤ በወይን አይይደለም፤ በጠጅም አይደለም። 10 እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስን አፍስሶባቸዋል፤ ዐይኖቻቸውን፥ የነቢያትንም ዐይን፥ የተሰወረውንም የሚያዩ የአለቆቻቸውን ዐይን ጨፍኖባቸዋል። 11 ይህም ሁሉ ነገር እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባቸዋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ፥ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፥ “ታትሟልና ማንበብ አልችልም” ይላቸዋል፤ 12 ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ፥ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፥ “ማንበብ አላውቅም” ይላቸዋል። 13 ጌታም አለ፥ “ይህ ሕዝብ በከንፈሮቹ ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በከንቱ ያመልኩኛል፤ ሰው ሠራሽ ትምህርትም ያስተምራሉ፤ 14 ስለዚህ፥ እነሆ፥ ይህ ሕዝብ በድጋሚ እንዲፈልስ አደርጋለሁ፤ አፈልሳቸዋለሁም፤ የጥበበኞችንም ጥበብ አጠፋለሁ፤ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እሰውራለሁ።” 15 ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ ወዮላቸው! ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው፥ “ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል?” ለሚሉ ወዮላቸው! 16 ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፥ “አልሠራኸኝም” ይለዋልን? ወይስ የተደረገ አድራጊውን፥ “በማስተዋል አላሳመርኸኝም” ይለዋልን? 17 ሊባኖስ እንደ ፍሬያማ እርሻ ሊለወጥ፥ ፍሬያማውም እርሻ እንደ ዱር ሊቈጠር ጥቂት ዘመን የቀረ አይይደለምን? 18 በዚያም ቀን ደንቆሮች የመጽሐፍን ቃል ይሰማሉ፤ በጨለማና በጭጋግ ውስጥም የዕውሮች ዐይኖች ያያሉ። 19 ነዳያን ደስታቸውን በእግዚአብሔር ያበዛሉ፤ በሰዎች መካከል ተስፋ የሌላቸውም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ ያደርጋሉ። 20 ኃጥእ ሰው አልቆአልና፥ ትዕቢተኛውም ጠፍቶአልና፥ በክፋት የበደሉም ሁሉ ይነቀላሉና፤ 21 እነዚህም ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፥ በበርም ለሚገሥጸው አሽክላ የሚያኖሩ፥ ጻድቁንም በከንቱ ነገር የሚያስቱ ናቸው። 22 ስለዚህ እግዚአብሔር ከአብርሃም ስለ ለየው ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፥ “ያዕቆብ አሁን አታፍርም፤ ፊትህም አሁን አይለወጥም። 23 ነገር ግን ልጆቻቸው የእጄን ሥራ ባዩ ጊዜ ስለ እኔ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፤ የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ። 24 በመንፈስም የሳቱ ማስተዋልን ያውቃሉ፤ የሚያጕረመርሙም መታዘዝን ይማራሉ፤ ዲዳ አንደበትም ሰላም መናገርን ይማራል።” |