ኤርምያስ 32 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤርምያስ የእርሻ መሬት እንደ ገዛ 1 በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዐሥረኛው ዓመተ መንግሥት፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በዐሥራ ስምንተኛው ዓመተ መንግሥት ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 በዚያ ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፤ ነቢዩ ኤርምያስም በይሁዳ ንጉሥ ቤት በነበረው በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ነበር። 3 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንዲህ ብሎ አስጠብቆት ነበርና፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ይቺን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ይይዛታል ብለህ ስለምን ትንቢት ትናገራለህ? 4 የይሁዳም ንጉሥ ሴዴቅያስ በእውነት በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፎ ይሰጣል፤ አፍ ለአፍም ይናገረዋል፤ ዐይን ለዐይንም ይተያያሉ እንጂ ከከለዳውያን እጅ አያመልጥም፤ 5 ሴዴቅያስም ወደ ባቢሎን ይገባል፤ እኔም እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይኖራል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከከለዳውያን ጋር ብቷጉ ምንም አይቀናችሁም።” 6 የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 7 “እነሆ የአጎትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፦ ትገዛው ዘንድ የመቤዠቱ መብት የአንተ ነውና በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ” ይልሃል። 8 እንደ እግዚአብሔርም ቃል የአጎቴ ልጅ አናምኤል እኔ ወደ አለሁበት ወደ ግዞቱ ቤት አደባባይ መጥቶ፥ “በብንያም ሀገር በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ፤ የመግዛትና የመውረስ መብቱ የአንተ ነውና፥ አንተ ታላቃችን ነህና፤ ለአንተ ግዛው” አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ ዐወቅሁ። 9 በዐናቶትም ያለውን እርሻ ከአጎቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፤ ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብርም መዘንሁለት። 10 የውሉንም ወረቀት ጻፍሁ፤ አተምሁትም፤ ምስክሮችንም ጠርቼ ብሩን በሚዛን መዘንሁለት። 11 የታተመውንም የውል ወረቀት ወሰድሁ፤ 12 የአጎቴም ልጅ አናምኤል፥ የውሉንም ወረቀት የፈረሙ ምስክሮች፥ በግዞት ቤት አደባባይ የተቀመጡ አይሁድም ሁሉ እያዩ የውሉን ወረቀት ለማሴው ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት። 13 በፊታቸውም እንዲህ ብዬ ባሮክን አዘዝሁት፦ 14 “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ብዙ ቀን ይጠበቅ ዘንድ የታተመውን ይህን የውል ወረቀት ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑረው። 15 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰዎች በዚህ ምድር ቤትንና እርሻን የወይን ቦታንም እንደ ገና ይገዛሉ።” የኤርምያስ ጸሎት 16 ለኔርያ ልጅ ለባሮክም የውሉን ወረቀት ከሰጠሁት በኋላ፥ እንዲህ ብዬ ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፦ 17 “ወዮ! አቤቱ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እነሆ አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ ከአንተም የሚሳን ምንም ነገር የለም። 18 ታላቅና ኀያል አምላክ ሆይ! ለብዙ ሺህ ምሕረትን ታደርጋለህ፤ የአባቶችንም በደል ከእነርሱ በኋላ በልጆቻቸው ብብት ትመልሳለህ። 19 እግዚአብሔር በምክር ታላቅ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ስምህ ታላቅ የሆነ፥ ኀያል፥ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ለሁሉም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ፍሬ ትሰጥ ዘንድ ዐይኖችህ በሰው ልጆች መንገድ ሁሉ ተገልጠዋል። 20 እስከ ዛሬም ድረስ ምልክትንና ድንቅን ነገር በግብፅ ምድር፥ ደግሞም በእስራኤልና በሌሎች ሰዎች መካከል አድርገሃል፤ እንደ ዛሬም ለአንተ ስም አድርገሃል። 21 በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፥ በታላቅም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብፅ ምድር አወጣህ። 22 ትሰጣቸውም ዘንድ ለአባቶቻቸው የማልህላቸውን ምድር፥ ወተትና ማርም የምታፈስሰውን ምድር ሰጠሃቸው፤ 23 እነርሱም ገብተው ወረሱአት፤ ነገር ግን ቃልህን አልሰሙም፤ በሕግህም አልሄዱም፤ ያደርጉም ዘንድ ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው። 24 አሕዛብም መጥተው ይህችን ሀገር ያዟት፤ ይህችም ከተማ ከረኃቡና ከጦሩ የተነሣ በወጓት በከለዳውያን ሰዎች እጅ ወደቀች፤ እንደ ተናገርኸውም ሆነ። 25 አንተም ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እርሻውን በብር ግዛ፤ ምስክሮችንም ጥራ አልኸኝ፤ እኔም ውሉን ጽፌ አተምሁ፤ ምስክሮችንም አቆምሁ፤ ከተማዪቱ ግን ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች።” 26 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 27 “እነሆ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ ከእኔ የሚሰወር ነገር አለን? 28 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ይችን ከተማ ለከለዳውያን እጅና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ይይዛታል። 29 ይችን ከተማ የሚወጉ ከለዳውያን ይመጣሉ፤ ከተማዋንም በእሳት ያነድዱአታል፤ ያስቈጡኝም ዘንድ በሰገነታቸው ላይ ለበዓል ያጠኑባቸውን፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን ያፈሰሱባቸውን ቤቶች ያቃጥሉአቸዋል። 30 የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች ከታናሽነታቸው ጀምሮ በፊቴ ክፉ ነገርን ብቻ አድርገዋልና፤ የእስራኤልም ልጆች እኔን በእጃቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ሥራ አላደረጉምና፥ ይላል እግዚአብሔር። 31 ከፊቴ አስወግዳት ዘንድ ይህች ከተማ ከሠሩአት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በቁጣዬና በመዓቴ ውስጥ ናትና፤ 32 ይህም እኔን ያስቈጡኝ ዘንድ፥ እነርሱና ነገሥታቶቻቸው፥ አለቆቻቸውም፥ ካህናቶቻቸውም፥ ነቢያቶቻቸውም፥ የይሁዳም ሰዎች፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ስለ አደረጉት ስለ እስራኤል ልጆችና ስለ ይሁዳ ልጆች ክፋት ሁሉ ነው። 33 ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ወደ እኔ መለሱ፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ሳስተምራቸው ተግሣጽን ይቀበሉ ዘንድ አልሰሙም። 34 ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ውስጥ ርኵሰታቸውን አኖሩ። 35 ይሁዳን ወደ ኀጢአት እንዲያገቡት፥ ይህን ርኵሰት ያደርጉ ዘንድ፥ እኔ ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን ነገር፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ በእሳት ያሳልፉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ያሉትን መሠዊያዎች ለበዓል ሠሩ።” አስተማማኝ ተስፋ 36 አሁን እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አንተ ስለ እርስዋ፥ “በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ትሰጣለች ስለምትላት ከተማ እንዲህ ይላል፦ 37 እነሆ በቍጣዬና በመዓቴ፥ በታላቅም መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁባት ሀገር ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ ተዘልለውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ 38 እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 39 ለእነርሱም፥ ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ለዘለዓለም እንዲፈሩኝ ሌላ መንገድና ሌላ ልብ እሰጣቸዋለሁ። 40 ከእነርሱም እንዳልመለስ፥ ከእነርሱ ጋር የዘለዓለምን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ። 41 ለእነርሱም መልካምን በማድረግ ይቅር እላቸዋለሁ፤ በእውነትም በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ። 42 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዳመጣሁ፥ እንዲሁ የተናገርሁላቸውን በጎነት ሁሉ አመጣላቸዋለሁ። 43 እናንተም፦ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ያለች ባድማ ናት፤ ለከለዳውያንም እጅ ተሰጥታለች በምትሉአት ምድር እርሻን እንደ ገና ይገዛሉ። 44 ምርኮኞቻቸውንም እመልሳለሁና በብንያም ሀገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች በደጋውም ባሉ ከተሞች፥ በቆላውም ባሉ ከተሞች፥ በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ ሰዎች እርሻውን በብር ይገዛሉ፤ በውሉም ወረቀት ፈርመው ያትማሉ፤ ምስክሮችንም ያቆማሉ፤” ይላል እግዚአብሔር። |