ኤርምያስ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የንስሐ ጥሪ 1 እስራኤል ወደ እኔ ቢመለስ ይመለስ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ርኵሰቱንም ከአፉ ቢያስወግድ፤ ከፊቴም የተነሣ ቢፈራ፥ 2 ሕያው እግዚአብሔርን! ብሎ በእውነትና በቅንነት፤ በጽድቅም ቢምል፥ አሕዛብ በእርሱ ይባረካሉ፤ በኢየሩሳሌምም እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። 3 እግዚአብሔር ለይሁዳ ወንዶችና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲህ ይላልና፦ ልባችሁን አድሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ። 4 እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳይነድ ለአምላካችሁ ተገረዙ፤ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ። ይሁዳን ለመውረር የተደረገ ዛቻ 5 በይሁዳ ዘንድ ተናገሩ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ አውሩና፦ በሀገሪቱ ላይ መለከት ንፉ በሉ፤ ጮኻችሁም፦ ሁላችሁ ተሰብሰቡ፤ ወደ ተመሸጉትም ከተሞች እንግባ በሉ። 6 ከሰሜን ክፉ ነገርንና ጽኑ ጥፋትን አመጣለሁና ዓላማችሁን አንሡ፤ ወደ ጽዮንም ሽሹ፥ ፍጠኑ፥ አትዘግዩ። 7 አንበሳ ከጕድጓዱ ወጥቶአል፤ አሕዛብንም ሊያጠፋቸው የሚዘርፍ ተነሥቶአል፤ ምድርሽን ባድማ ያደርግ ዘንድ፥ ከተሞችሽንም ሰው እንዳይኖርባቸው ያፈርሳቸው ዘንድ ከስፍራው ወጥቶአል። 8 የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ከእኛ ዘንድ አልተመለሰምና ማቅ ልበሱ፤ አልቅሱም፤ ዋይም በሉ። 9 በዚያም ቀን ይላል እግዚአብሔር፤ የንጉሡና የመኳንንቱ ልብ ይጠፋል፤ ካህናቱም ይደነግጣሉ፤ ነቢያቱም ያደንቃሉ። 10 እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! አንተ ሰይፍ እስከ ሰውነታቸው ድረስ እስክትደርስ ሰላም ይሆንላችኋል” ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን እጅግ አታለልህ አልሁ። 11 በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይሏቸዋል፦ በምድረ በዳ የሚያስት ጋኔን አለ፤ የሕዝቤ ሴት ልጅ መንገድም ለንጽሕና ወይም ለቅድስና አይደለም። 12 አሳች ጋኔን ይመጣል፤ አሁንም እኔ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። 13 እነሆ! እንደ ደመና ይወጣል፤ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤ ፈረሶቹም ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። ተዋርደናልና ወዮልን። 14 ኢየሩሳሌም ሆይ! ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ አሳብ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ነው? 15 የወሬ ነጋሪ ድምፅ ከዳን ይመጣል፥ ከኤፍሬምም ተራሮች መከራ ይሰማል። 16 ለአሕዛብ አሳስቡ፥ “እነሆ፥ መጡ! ጠላቶች ከሩቅ ሀገር ይመጣሉ፤ በይሁዳም ከተሞች ላይ ይጮኻሉ ብላችሁ በኢየሩሳሌም ላይ አውጁ። 17 በእኔ ላይ ዐመፀኛ ሆናለችና በዙሪያዋ ከብበው እንደ እርሻ ጠባቂዎች ሆነውባታል” ይላል እግዚአብሔር። 18 መንገድሽና ክፉ ሥራሽ ይህን አድርጎብሻል፤ ይህ ክፋትሽ መራራ ነው፤ ወደ ልብሽም ደርሶአል። ስለ ሕዝቡ የኤርምያስ ኀዘን 19 አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል፤ ነፍሴም አእምሮዋን አጥታለች፤ በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል፤ ነፍሴም የመለከትን ድምፅና የሰልፍን ውካታ ሰምታለችና ዝም እል ዘንድ አልችልም። 20 መከራ በመከራ ላይ ተጠርቶአል፤ ምድር ሁሉ ተዋርዳለችና፤ በድንገትም ድንኳኔ ጠፋ፤ መጋረጃዎችም ተቀዳደዱ። 21 የሚሸሹትን የምመለከት፥ የመለከቱንስ ድምፅ የምሰማ እስከ መቼ ነው? 22 የሕዝቤ አለቆች አላወቁኝም፤ እነርሱ ሰነፎች ልጆች ናቸው፤ ማስተዋልም የላቸውም፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልሃተኞች ናቸው፤ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም። 23 ምድሪቱን ተመለከትሁ፤ እነሆም ባዶ ነበረች፤ ሰማያትንም ተመለከትሁ፤ ብርሃንም አልነበረበትም። 24 ተራሮችን ተመለከትሁ፤ እነሆም ይንቀጠቀጡ ነበር፤ ኮረብቶችም ሁሉ ይናወጡ ነበር። 25 ተመለከትሁ፤ እነሆም ሰው አልነበረም፤ የሰማይም ወፎች ሁሉ ሸሽተው ነበር። 26 ተመለከትሁ፤ እነሆም ቀርሜሎስ ምድረ በዳ ሆነች፤ ከተሞችም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ በእሳት ተቃጠሉ፤ ከጽኑ ቍጣውም የተነሣ ፈጽመው ጠፉ። 27 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ምድር ሁሉ ባድማ ትሆናለች፤ ነገር ግን ፈጽሜ አላጠፋትም። 28 ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፤ በላይም ሰማይ ይጠቍራል፤ ተናግሬአለሁና፤ አልጸጸትም ወደፊት እሮጣለሁ፤ ከእርስዋም አልመለስም። 29 ከፈረሰኞችና ከቀስተኞች ድምፅ የተነሣ ሀገሯ ሁሉ ሸሽታለች፤ ወደ ዋሻዎች ይገባሉ፥ በዛፍ ሥር ተሸሸጉ፥ በቋጥኝም ላይ ይወጣሉ፤ ከተማዋ ሁሉ ተለቅቃለች፤ የሚቀመጥባትም ሰው የለም። 30 አንቺስ ምን ታደርጊያለሽ? ቀይ በለበስሽ ጊዜ፥ በወርቅ አንባርም ባጌጥሽ ጊዜ፥ ዐይንሽንም በኵል በተኳልሽ ጊዜ፥ በከንቱ ታጌጫለሽ፤ ፍቅረኞችሽ አቃለሉሽ፥ ነፍስሽን ይሹአታል። 31 እንደምታምጥ፥ የበኵር ልጅዋንም እንደምትወልድ ሴት ጩኸት፥ ጩኸትሽን ሰምቻለሁና፤ የጽዮን ሴት ልጅ ድምፅ በድካም ሰለለ፤ እጆችዋንም ትዘረጋለች፤ ተገድለው ከሞቱት የተነሣ ነፍሴ ዝላለችና ወዮልኝ! አለች። |