ኢሳይያስ 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ምድረ በዳ አይደለችምን? 2 ጫጩቶችዋን አሳድጋ እንደ ተወች ወፍ ሆናለችና፤ የሞዓብ ሴት ልጅም እንደ ሰባ የበግ ጠቦት ሆነች። 3 አርኖንም በምትኖርበት ምሽግ መጠለያን ትሠራ ዘንድ ብዙ ትመክራለች፤ በቀትር ጊዜ እንደ ሌሊት ደንግጠው ይሸሻሉ፤ ወደ እናንተም አታስገቡአቸው። 4 ከሚከቧችሁ ጋር ጠላቶች እንዳይሆኗችሁ ከሞዓብ የተሰደዱትን ከእናንተ ጋር አታስቀምጡ፤ ሰልፈኞች አልቀዋልና፤ በሀገሪቱ ሁሉ የነበረውም አለቃ ጠፍቶአልና። 5 ዙፋን በምሕረት ይጸናል፥ በዚያም ላይ በዳዊት ቤት ፍርድን የሚሻ ጽድቅንም የሚያፋጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል፤ ይፈርዳልም። 6 የሞዓብን ትዕቢትና እጅግ መኵራቱን ሰምተናል፤ ትዕቢቱንም አስወገድሁ፤ ጥንቈላህ እንዲህ አይደለምና፥ እንዲህም አይደለም፤ 7 ሞዓብ ዋይ በሉ፤ ሁሉም በሞዓብ ዋይ ይላሉና፤ በዴሴት የሚኖሩም አያመልጡም፤ ጠብን ያጭራሉ፤ ያፍራሉም። 8 የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች እስከ ኢያዜር ደርሰው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፤ ቍጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር። 9 ስለዚህ በኢያዜር ልቅሶ ስለ ሴባማ ወይን ግንድ አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ ዛፎችሽ ወድቀዋል፤ የዛፍሽን ፍሬና የወይንሽን መከር እረግጣለሁ፤ ተክሎችሽ ሁሉ ይወድቃሉ። 10 ደስታና ሐሤትም ከወይን ቦታሽ ተወስዶአል፤ በወይንሽም ቦታዎች ፈጽመው ደስ አይላቸውም፤ በመጥመቂያውም ወይንን አይረግጡም፤ ረጋጮቹን አጥፍቻለሁና። 11 ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ እንደ መሰንቆ ትጮኻለች። አጥንቶችም እንደ ተመረገ ግድግዳ ይሆናሉ። 12 ለኀፍረት ይሆንብሃል፤ ሞዓብ በመሠዊያዎችዋ ደክማለችና፤ ለጸሎትም ወደ ጣዖቶችዋ ትሄዳለች፤ ሊያድኑአትም አይችሉም። 13 እግዚአብሔር በሞዓብ ላይ በድሮ ዘመን የተናገረው ነገር ይህ ነው። 14 አሁንም እንዲህ እላለሁ፤ በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምንደኛ ዓመት የሞዓብ ክብር ከብዙ ሀብትዋ ጋር ይዋረዳል፤ በቍጥርም ጥቂት ይቀራል፤ ክብርዋም አይገኝም። |