ዕዝራ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም መውጣት 1 ከዚህም ነገር በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርተሰስታ መንግሥት ዕዝራ የሠራያ ልጅ፥ የዓዛርያስ ልጅ፥ የኬልቅያስ ልጅ፥ 2 የሰሎም ልጅ፥ የሳዶቅ ልጅ፥ የአኪጦብ ልጅ፥ 3 የአማርያ ልጅ፥ የዓዛርያስ ልጅ፥ የመራዮት ልጅ፥ 4 የዘራእያ ልጅ፥ የኡዚ ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥ 5 የአቢሱ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የአልዓዛር ልጅ፥ የመጀመሪያው ካህን የአሮን ልጅ፥ 6 ይህም ዕዝራ ከባቢሎን ወጣ፤ እርሱም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ሕግ ዐዋቂ ነበረ፤ የአምላኩም የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና ንጉሡ ያሻውን ሁሉ ሰጠው። 7 ከእስራኤልም ልጆች ከካህናቱም፥ ከሌዋውያኑም፥ ከመዘምራኑም፥ ከበረኞቹም፥ ከናታኒምም በንጉሡ በአርተሰስታ በሰባተኛው ዓመት ዐያሌዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 8 በንጉሡም በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። 9 በመጀመሪያውም ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን ሊወጡ ጀመሩ፤ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና በአምስተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። 10 ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፥ ለእስራኤልም ሥርዐትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር። ከንጉሡ አርተሰስታ ለዕዝራ የተሰጠ ፈቃድ 11 ንጉሡም አርተሰስታ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ቃልና ለእስራኤል የሆነውን ሥርዐት ይጽፍ ለነበረው ለጸሓፊው ለካህኑ ለዕዝራ የሰጠው የደብዳቤው ቃል ይህ ነው፦ 12 “ከንጉሠ ነገሥት ከአርተሰስታ ለሰማይ አምላክ ሕግ ጸሓፊ ለካህኑ ለዕዝራ፥ ሰላም ይሁን፤ 13 በመንግሥቴም ውስጥ ካሉ ከእስራኤል ሕዝብ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ የሚወድድ ሁሉ ከአንተ ጋር እንዲሄድ አዝዣለሁ። 14 ንጉሡና ሰባቱ አማካሪዎቹ በእጅህ እንዳለችው እንደ አምላክህ ሕግ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ትጐበኝ ዘንድ አዝዘዋል፤ 15 ንጉሡና አማካሪዎቹም መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው ያቀረቡትን ብርና ወርቅ፥ 16 በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ የምታገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤት በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ትወስድ ዘንድ አዝዘዋል፤ 17 ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ ያዘዝሁህ ትእዛዝ ይህ ነው። በዚህ ገንዘብ ወይፈኖችንና አውራ በጎችን፥ ጠቦቶችንም፥ የእህላቸውንና የመጠጣቸውን ቍርባን ተግተህ ግዛ፤ በኢየሩሳሌምም ባለው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው። 18 ከቀረውም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ ለማድረግ ደስ የሚያሰኛችሁን ነገር እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አድርጉ። 19 ስለ አምላክህም ቤት አገልግሎት የተሰጠህን ዕቃ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አሳልፈህ ስጥ። 20 ከዚህም በላይ ለማውጣት የሚያስፈልግህን ለአምላክህ ቤት የሚያሻውን ነገር ከንጉሡ ቤተ መዛግብት ስጥ። 21 እኔም ንጉሡ አርተሰስታ በወንዝ ማዶ ላሉት ግምጃ ቤቶች ሁሉ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፦ የሰማይ አምላክ ሕግ ጸሓፊ ካህኑ ዕዝራ ከእናንተ የሚፈልገውን ሁሉ አዘጋጁለት፤ 22 እስከ መቶ መክሊት ብርም ቢሆን፥ እስከ መቶም የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት ቢሆን፥ ጨውም ያለ ልክ ቢሆን፤ 23 በንጉሡ መንግሥትና በልጆቹ ላይ ቍጣ እንዳይሆን፥ የሰማይ አምላክ ያዘዘው ሁሉ ይደረግ፤ ለሰማይ አምላክ ቤት የታዘዘውንም እንዳታቋርጡ ተጠንቀቁ። 24 ደግሞም በካህናቱና በሌዋውያኑ፥ በመዘምራኑም፥ በበረኞቹም፥ በናታኒምም በዚህም በእግዚአብሔር ቤት በሚሠሩ አገልጋዮች ላይ ግብርና ቀረጥ እንዳይጣል፥ የምትገዙአቸውም አገዛዝ እንዳይኖር ብለን እናስታውቃችኋለን። 25 አንተም ዕዝራ፥ በእጅህ እንዳለው እንደ አምላክህ ጥበብ መጠን በወንዝ ማዶ ባሉ ሕዝብ ሁሉ፥ የአምላክህን ሕግ በሚያውቁ ሁሉ ላይ ይፈርዱ ዘንድ ጻፎችንና ፈራጆችን ሹም፤ የማያውቁትንም አስተምሩአቸው። 26 የአምላክህንም ሕግ፥ የንጉሡንም ሕግ በማያደርግ ሁሉ ላይ ሞት፥ ወይም ስደት፥ ወይም ገንዘብ መወረስ፥ ወይም ግዞት በፍጥነት ይፈረድበት።” 27 ያባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ያከብር ዘንድ ይህን ነገር በንጉሡ ልብ ያኖረ፥ 28 በንጉሡ ፊት በሚመክሩትም፥ በኀያላኑም፥ በንጉሡ አለቆች ሁሉ ፊት በእኔ ላይ ምሕረቱን ላከ። እኔም በእኔ ላይ ባለችው በአምላኬ በእግዚአብሔር እጅ በረታሁ፤ ከእኔም ጋራ ይወጡ ዘንድ ከእስራኤል አለቆቹን ሰበሰብሁ። |