ዘፀአት 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በግብፅ በእስራኤላውያን ላይ የደረሰው ግፍዕ 1 ከአባታቸው ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፤ ሰው ሁሉ ከቤተ ሰቡ ጋር ገባ፤ 2 ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ 3 ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ ብንያም። 4 ዳን፥ ንፍታሌም፥ ጋድ፥ አሴር። 5 ዮሴፍም አስቀድሞ በግብፅ ነበረ። ከያዕቆብ ጕልበት የወጡት ሰዎች ሁሉ ሰባ ነፍሶች ነበሩ፤ 6 ዮሴፍም ሞተ፤ ወንድሞቹም፥ ያም ትውልድ ሁሉ። 7 የእስራኤልም ልጆች በዙ፤ ተባዙም፤ የተጠሉም ሆኑ። እጅግም ጸኑ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች። 8 በግብፅ ዮሴፍን ያላወቀ ሌላ ንጉሥ ተነሣ። 9 እርሱም ሕዝቡን፥ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሕዝብ ታላቅና ብዙ ሆነዋል፤ ከእኛም ይልቅ በርትተዋል፤ 10 ኑ፤ እንጠበብባቸው፤ የበዙ እንደሆነ ጦርነት በመጣብን ጊዜ በጠላቶቻችን ላይ ተደርበው በኋላችን ይወጉናልና፥ ከምድራችንም ያስወጡናልና።” 11 በብርቱ ሥራም ያስጨንቋቸው ዘንድ የሠራተኞች አለቆችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፌቶምን፥ ራምሴንና የፀሐይ ከተማ የምትባል ዖንን ጽኑ ከተሞች አድርገው ሠሩ። 12 ነገር ግን እንዳስጨነቁአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፤ እጅግም ጸኑ ፤ ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች ይጸየፉአቸው ነበር። 13 ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች በግፍዕ ገዙአቸው። 14 በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡብም፥ በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፤ ሕይወታቸውን ያስመርሩአቸው ነበር። 15 የግብፅም ንጉሥ አንዲቱ ሲፓራ፥ ሁለተኛዪቱም ፎሓ የሚባሉትን የዕብራውያትን አዋላጆች እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ 16 “እናንተ ዕብራውያትን ሴቶች ስታዋልዱ ለመውለድ እንደ ደረሱ በአያችሁ ጊዜ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት፤ ሴት ብትሆን ግን አትግደሏት።” 17 አዋላጆች ግን እግዚአብሔርን ፈሩ፤ የግብፅ ንጉሥም እንደ አዘዛቸው አላደረጉም፤ ወንዶቹን ሕፃናትንም አዳኑአቸው። 18 የግብፅም ንጉሥ አዋላጆችን ጠርቶ፥ “ለምን እንዲህ አደረጋችሁ? ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን አዳናችሁ?” አላቸው። 19 አዋላጆችም ፈርዖንን፥ “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፅ ሴቶች ስላልሆኑ አዋላጆች ሳይገቡ ይወልዳሉ” አሉት። 20 እግዚአብሔርም ለአዋላጆች መልካም አደረገላቸው፤ ሕዝቡም በዙ፤ እጅግም ጸኑ። 21 እንዲህም ሆነ፤ አዋላጆች እግዚአብሔርን ስለፈሩ ቤቶችን አደረገላቸው። 22 ፈርዖንም፥ “የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ወንዝ ጣሉት፤ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት አድኑአት” ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ። |