Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa

መጽሐፈ ሄኖክ 42 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)

1 ለልጁ ለማቱሳላ፥ ከእርሱም በኋላ ለሚመጡና በኋላ ዘመን ሥርዐቱን ለሚጠብቁ ሰዎች ሄኖክ የጻፈው ሁለተኛ መጽሐፍ ይህ ነው።

2 ክፉውን ሥራ የሚሠሩ ሰዎች እስኪጨረሱ ድረስ፥ የበደለኞችም ሠራዊት እስኪፈጸም ድረስ መልካም የሠራችሁ እናንተ፥ በእነዚያ ወራቶች ትቈያላችሁ።

3 እናንተ ግን ኀጢአት እስክታልፍ ድረስ ደጅ ጥኑ። ስማቸው ቅዱሳን ከተጻፉበት መጽሐፍ ይፋቅ ዘንድ አለውና፥ ዘራቸውም ለዘላለም ይጠፋልና። ልጆቻቸውም ይሞታሉ፥ በማይታይም ምድረ በዳ ጮኸው ያለቅሳሉ፤ በእሳትም ይቃጠላሉ፥ በዚያ ምድር የለምና። ከጥልቅነቱ የተነሣ ወደ ላይ ማየትን አልቻልሁምና በዚያ ቦታ እንደማይታይ ደመና ያለ ነገርን አየሁ።

4 የእሳቱም ወላፈን ሲነድ አየሁት፥ የሚበራም ነበር፤ እንደሚያበሩ ተራሮችም የተከበቡ ነገሮች ነበሩ፥ ወዲያና ወዲህም ይታወካሉ።

5 ከእኔ ጋር ካሉ ከቅዱሳን መላእክት አንዱን ጠየቅሁት፥ እንዲህም አልሁት- “ይህ የሚያበራው ምንድን ነው? ሰማይ አይደለምና፥ ነገር ግን ብቻውን የሚነድድ የእሳት ወላፈን፥ የጩኸትና የልቅሶ፥ የዋይታና የብርቱ ሕማም ቃል ነው።”

6 እርሱም እንዲህ አለኝ- “ይህ የምታየው ቦታ የኃጥኣንና የተሳዳቢዎች፥ ኀጢኣትን የሚሠሩ፥

7 እግዚአብሔር በነቢያት አንደበት ያናገራቸውን በምድር ላይ ይደረጉ ዘንድ ያላቸውን ሁሉ የሚለውጡ ሰዎች ነፍሳት የሚጣሉበት ቦታ ነው።

8 መላእክት ያነብቧቸው ዘንድ፥ በኃጥኣንና በተዋረዱትም ሰዎች መናፍስት ይደርስባቸው ዘንድ ያለውን ያውቁ ዘንድ ከእነርሱ ወገን በላይ በሰማይ የተጻፉና የተቀረጹ አሉና።

9 ነገር ግን ሥጋቸውን መከራ ያስቻሉ፥ ከፈጣሪም ዘንድ ዋጋ የተቀበሉ፥ ከክፉ ሰዎችም የተነሣ የተዋረዱ፥ ፈጣሪያቸውንም የወደዱ ወርቅና ብርን፥ በዚህም ዓለም ያለውን በጎ ነገር ሁሉ አይወዱም፤ ነገር ግን ሥጋቸውን ለመከራ ሰጡ፤ ከተፈጠሩም ጀምሮ በዚህ ዓለም ያሉ መብሎችን ያልተመኙ ራሳቸውን እንደ ሞተች ሰውነት አደረጉ። ይህንም ጠበቁ፥ ጌታም ብዙ ጊዜ ፈተናቸው፤ ስሙንም ያመሰግኑ ዘንድ ሰውነቶቻቸው በንጽሕና ተገኙ።

10 በረከታቸውንም ሁሉ በመጻሕፍት ተናገርሁ፤ እኒህ ከዘለዓለማዊ ሕይወታቸው ጀምሮ ሰማያዊውን ሲወዱት፥

11 ከክፉ ሰዎችም መከራን ሲቀበሉ፥ ከእነርሱም ተግዳሮትንና ስድብን ሲሰሙ፥ እያመሰገኑኝም ሲጐሳቈሉ ተገኝተዋልና ለእየራሳቸው ዋጋቸውን ሰጣቸው።

12 አሁንም ከብርሃን ልጆች የተወለዱ የደጎችን ነፍሳት እጠራለሁ፥ ለሃይማኖታቸው እንደሚገባ በሥጋቸው ክብርን ላልተቀበሉና በጨለማ ለተወለዱ እለውጣለሁ።

13 ቅዱስ ስሜንም የወደዱትን በብሩህ ብርሃን አወጣቸዋለሁ፤ እያንዳንዱንም እንደ ክብሩ በክብር ዙፋን አስቀምጠዋለሁ፥ የአምላክም ፍርድ እውነት ነውና ቍጥር በሌላቸው ዘመኖች ያበራሉ።

14 በቅን መንገዶች ማደሪያ ለምእመናን ሃይማኖትን ይሰጣቸዋልና።

15 ጻድቃን እያበሩ በጨለማ የተወለዱትን በጨለማ ሲጣሉ ያዩአቸዋል፤ ኃጥኣንም እየጮኹ ጻድቃንን ሲያበሩ ያዩአቸዋል።

16 እነርሱም በተጻፉላቸው ቀኖችና ዘመኖች ይኖራሉ። የሄኖክ ስውር ራእይ ተፈጸመ፥ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፥ ለዘለዓለም አሜን።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos