ዘዳግም 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “በሰዎች መካከል ጠብ ቢሆን፥ ወደ ፍርድም ቢመጡ፥ ቢፋረዱም ለጻድቁ ይፈረድለት፤ በበደለኛውም ይፈረድበት። 2 በደለኛውም መገረፍ ቢገባው እንዲገረፍ ፈራጁ በፊቱ በምድር ላይ ያጋድመው፤ የግርፋቱም ቍጥር እንደ ኀጢአቱ መጠን ይሁን። 3 ግርፋቱም አርባ ይሁን፤ ከዚህ በላይ ጨምሮ ብዙ ግርፋት ቢገርፈው ወንድምህ በፊትህ ነውረኛ ይሆናልና ከዚህ በላይ አይጨመርበት። 4 “እህልህን በምታበራይ ጊዜ በሬዉን አፉን አትሰረው። ወንድም፥ ለሞተ ወንድሙ የሚያደርገው ግዴታ 5 “ወንድማማቾች በአንድነት ቢቀመጡ፥ አንዱም ልጅ ሳይኖረው ቢሞት፥ የሞተው ሰው ሚስት ሌላ ሰው ታገባ ዘንድ ወደ ውጭ አትሂድ፤ ነገር ግን የባልዋ ወንድም ወደ እርስዋ ገብቶ እርስዋን ያግባ፤ ከእርስዋም ጋር ይኑር። 6 የምዋቹ ስም ከእስራኤል ዘንድ እንዳይጠፋ ከእርስዋ የሚወለደው ልጅ በሞተው በወንድሙ ስም ይጠራ። 7 ያም ሰው የወንድሙን ሚስት ማግባት ባይወድድ፥ ዋርሳዪቱ በበሩ አደባባይ ወደሚቀመጡ ሽማግሌዎች ሄዳ፦ ‘ዋርሳዬ በእስራኤል ዘንድ ለወንድሙ ስም ማቆም እንቢ አለ፤ ከእኔም ጋር ሊኖር አልወደደም’ ትበላቸው። 8 የከተማውም ሽማግሌዎች ጠርተው ይጠይቁት፤ እርሱም በዚያ ቆሞ፦ ‘አገባት ዘንድ አልወድድም’ ቢል፥ 9 ዋርሳዪቱ በሽማግሌዎቹ ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፦ ‘የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ይደረግበታል’ ስትል የአንድ እግሩን ጫማ ታውጣ፤ በፊቱም እንትፍ ትበልበት። 10 በእስራኤልም ዘንድ ስሙ ‘የጫማ ፈቱ ቤት’ ተብሎ ይጠራ። ልዩ ልዩ ትእዛዛት 11 “ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ የአንደኛውም ሰው ሚስት ባልዋን ከሚመታው ሰው እጅ ታድነው ዘንድ ብትቀርብ፥ እጅዋንም ዘርግታ ሁለቱን የብልቱን ፍሬዎች ብትይዝ፥ 12 እጅዋን ቍረጥ፤ ዐይንህም አትራራላት። 13 “በከረጢትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ ሚዛን አይኑርልህ። 14 በቤትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ መስፈሪያ አይኑርልህ። 15 አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ እውነተኛና ፍጹም ሚዛን ይሁንልህ፤ እውነተኛና ፍጹም መስፈሪያም ይሁንልህ። 16 ይህን የሚያደርግ ሁሉ፥ ክፋትንም የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና። ዐማሌቃውያንን ስለ ማጥፋት የተሰጠ ትእዛዝ 17 “ከግብፅ በወጣህ ጊዜ ዐማሌቅ በመንገድ ላይ ያደረገብህን ዐስብ፤ 18 በመንገድ ላይ እንደ ተቃወመህ፥ አንተም ተርበህና ደክመህ ሳለህ ጓዝህንና ከአንተ በኋላ ደክመው የነበሩትን ሁሉ እንደ መታ፤ እግዚአብሔርንም አልፈራውም። 19 ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር ከሚከብቡህ ጠላቶችህ ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ባሳረፈህ ጊዜ፥ የዐማሌቅን ዝክረ ስሙን ከሰማይ በታች አጥፋው፤ ይህንም አትርሳ። |