ዘዳግም 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የመማጠኛ ከተሞች ( ዘኍ. 35፥9-28 ፤ ኢያ. 20፥1-9 ) 1 “አምላክህ እግዚአብሔር ምድራቸውን የሚሰጥህን አሕዛብ ባጠፋቸው ጊዜ፥ በወረስሃቸውም ጊዜ፥ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፥ 2 አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በምድርህ መካከል ሦስት ከተሞችን ለራስህ ትለያለህ። 3 ለአንተም መንገድህን ታዘጋጃለህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር የሚያወርስህን ምድር ከሦስት አድርገህ ትከፍላለህ፤ ለነፍሰ ገዳይም ሁሉ መማጸኛ ይሁን። 4 “የነፍሰ ገዳይ ሕግ ይህ ነው፤ ቀድሞ ጠላቱ ሳይሆን ባልንጀራውን ሳያውቅ የገደለ ወደዚያ ሸሽቶ በሕይወት ይኑር። 5 ሰው ከባልንጀራው ጋር እንጨት ሊለቅም ወደ ዱር ቢሄድ፥ ዛፉንም ሲቈርጥ ምሳሩ ከእጁ ቢወድቅ፥ ብረቱም ከእጄታው ቢወልቅ፥ በባልንጀራውም ላይ ቢወድቅና ቢገድለው፥ ከእነዚህ ከተሞች በአንዲቱ ተማጥኖ በሕይወት ይኖራል፤ 6 ባለ ደሙ ነፍሰ ገዳዩን በልቡ ተናድዶ እንዳያሳድደው መንገዱም ሩቅ ስለሆነ አግኝቶ እንዳይገድለው፥ አስቀድሞ ጠላቱ አልነበረምና ሞት አይገባውም። 7 ስለዚህ እኔ፦ ለአንተ ሦስት ከተሞችን ለይ ብዬ አዝዤሃለሁ። 8 አምላክህም እግዚአብሔር ለአባቶችህ እንደ ማለላቸው ዳርቻህን ቢያሰፋ፥ ለአባቶችህ እሰጣቸዋለሁ ብሎ የተናገረውን ምድር ሁሉ ቢሰጥህ፥ 9 አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ ሁልጊዜም በመንገዱ ሁሉ ትሄድ ዘንድ፥ ዛሬ የማዝዝህን ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ታደርጋት ዘንድ ብትሰማ፥ በእነዚህ በሦስት ከተሞች ላይ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትጨምራለህ። 10 አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ንጹሕ ደም እንዳይፈስስ፥ በውስጥህም የደም ወንጀለኛ እንዳይኖር። 11 “ሰው ግን ባልንጀራውን ቢጠላ፥ ቢሸምቅበትም፥ በእርሱም ላይ ቢነሣ፥ ቢገድለውም፥ ከእነዚህ ከተሞች በአንዲቱ ቢማጠን፥ 12 የከተማው ሽማግሌዎች ይልካሉ፤ ከዚያም ይይዙታል። በባለደሙም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል፤ ይሞታልም። 13 ዐይንህም አትራራለት፤ ነገር ግን ንጹሑን ደም ከእስራኤል ታስወግዳለህ፤ መልካምም ይሆንልሃል። ድንበር ማፍረስ እንደማይገባ 14 “አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር፤ በምትካፈላት ርስትህ አባቶችህ የተከሉትን የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አትንቀል። ስለ ምስክሮች የተሰጠ መመሪያ 15 “ስለ በደል ሁሉ፥ ክፉ በማድረግም ስለሚሠራት ኀጢአት ሁሉ በማንም ላይ አንድ ምስክር አይሁን፤ በሁለት ምስክሮች ወይም በሦስት ምስክሮች ቃል ነገር ሁሉ ይጸናል። 16 በዐመፃ ይከስሰው ዘንድ በሰው ላይ ሐሰተኛ ምስክር ቢቆም፥ 17 ሁለቱ ጠበኞች በእግዚአብሔር ፊት በካህናቱና በዚያ ዘመን በሚፈርዱ ፈራጆች ፊት ይቆማሉ፤ 18 ፈራጆቹም አጥብቀው ይመረምራሉ፤ ያም ምስክር ሐሰተኛ ምስክር ሆኖ በወንድሙ ላይ በሐሰት ተናግሮ ቢገኝ፥ 19 በወንድሙ ላይ ክፋትን ያደርግ ዘንድ እንደ ወደደ በእርሱ ላይ ታደርጉበታላችሁ፤ እንዲሁም ከእናንተ መካከል ክፉውን ታስወግዳላችሁ። 20 ሌላውም ሰምቶ ይፈራል፤ እንደዚህ ያለውንም ክፋት በመካከልህ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ አያደርግም። 21 ዐይንህም አትራራለት፤ ነፍስ በነፍስ፥ ዐይን በዐይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥ እግር በእግር ይመለሳል። |