ዘዳግም 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዕዳ የሚሠረዝበት ዓመት ( ዘሌ. 25፥1-7 ) 1 “በየሰባቱ ዓመት የዕዳ ምሕረትን ታደርጋለህ። 2 ለምሕረቱም የሚገባ ትእዛዝ ይህ ነው፤ ባልንጀራህ ወይም ወንድምህ የሚከፍልህን ገንዘብ ሁሉ አትከፈል፤ የአምላክህ የእግዚአብሔር ምሕረት ተብላለችና። 3 ከባዕድ ግን በእርሱ ዘንድ ያለህን ሁሉ መቀበል ትችላለህ፤ በወንድምህ ላይ ያለውን ሁሉ ግን ተውለት። 4 አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ አምላክህ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይባርክሃልና በመካከልህ ድሃ አይኖርም፤ 5 አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመህ ብትሰማ፥ ታደርጋትም ዘንድ ዛሬ የማዝዝህን ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቅ፥ 6 አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ነገረህ ይባርክሃል፤ ለብዙ አሕዛብም ብዙ ታበድራለህ፤ አንተ ግን አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብንም ትገዛለህ፤ አንተን ግን አይገዙህም። 7 “አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ ምድር ካሉ ከተሞች በአንዲትዋ ውስጥ ከሚኖሩ ከወንድሞችህ አንዱ ቢቸገር ልብህን አታጽና፤ ለወንድምህ ከመስጠት እጅህን አትመልስ። 8 ነገር ግን እጅህን ለእርሱ ዘርጋ፤ የለመነህንም ሁሉ ስጠው። 9 ሰባተኛው ዓመት የምሕረት ዓመት ቅርብ ነው፤ አልሰጠውምም ብለህ ክፉ ዐሳብ በልብህ እንዳታስብ ለራስህ ዕወቅ። ወንድምህም ዐይኑን በአንተ ላይ ያከፋል፤ እርሱም ወደ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ይጮሃል፤ ኀጢአትም ይሆንብሃል። 10 እጅህን በምትጥልበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ስለዚህ በሥራህ ሁሉ ይባርክሃልና ፈጽመህ ስጠው፤ የለመነህንም ያህል አበድረው፤ በሰጠኸውም ጊዜ በልብህ አትጸጸት። 11 ድሃ ከምድርህ ላይ አይታጣምና ስለዚህ እኔ፦ በሀገርህ ውስጥ ላለው ድሃ፥ ለሚለምንህም ወንድምህ እጅህን ዘርጋ ብዬ አዝዝሃለሁ። ባሮች ነጻ የሚወጡበት ዓመት ( ዘፀ. 21፥1-11 ) 12 “አንተም ወንድምህን ዕብራዊዉን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግሉህ፤ በሰባተኛውም ዓመት ከአንተ ዘንድ አርነት አውጥተህ ልቀቀው። 13 ከአንተም ዘንድ አርነት አውጥተህ በለቀቅኸው ጊዜ ባዶውን አትልቀቀው። 14 ነገር ግን ከበጎችህ፥ ከእህልህም፥ ከወይንህም መጭመቂያ ስንቅ ትሰንቅለታለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ባረከህ መጠን ትሰጠዋለህ። 15 አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደ ነበርህ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከዚያ እንዳዳነህ ዐስብ፤ ስለዚህ እኔ ዛሬ ይህን ነገር አዝዝሃለሁ። 16 እርሱ ግን አንተንና ቤትህን ስለ ወደደ፥ በአንተም ዘንድ መኖር መልካም ስለሆነለት፦ ‘አልወጣም’ ቢል፥ 17 አንተ ወስፌ ወስደህ በቤትህ በር ላይ ጆሮውን ትበሳዋለህ፤ ለዘለዓለምም ባሪያ ይሆንልሃል። በሴት ባሪያህም ደግሞ እንዲሁ ታደርጋለህ። 18 እርሱንም አርነት ባወጣኸው ጊዜ የምንደኝነቱን ሥራ ሁለት ዕጥፍ አድርጎ ስድስት ዓመት አገልግሎሃልና አያስጨንቅህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር በምትሠራው ሁሉ ይባርክሃል። የእንስሳት በኵራት 19 “ላምህና በግህ የወለዱትን ተባት የሆነውን በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ትቀድሳለህ፤ በበሬህ በኵራት አትሥራበት፤ የበግህንም በኵራት አትሸልት። 20 አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ አንተና ቤተ ሰብህ በየዓመቱ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብላው። 21 ነውረኛ ወይም አንካሳ ወይም ዕውር ቢሆን፥ ወይም አንዳች ክፉ ነውር ቢኖረው፥ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋው። 22 በሀገርህ ውስጥ ትበላዋለህ፤ ንጹሕ ሰው፥ ንጹሕም ያልሆነ፥ ሚዳቋንና ዋሊያን እንደሚበሉ ይበሉታል። 23 ነገር ግን ደሙን በምድር ላይ እንደ ውኃ አፍስሰው እንጂ አትብላው። |