አሞጽ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ራእይ ስለ አንበጣ 1 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም ከምሥራቅ አንበጣ ይመጣል፤ አንዱም ኵብኵባ ንጉሡ ጎግ ነበረ። 2 የምድሩንም ሣር በልቶ ይጨርሳል፤ እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብን ማን ያነሣዋል? ጥቂት ነውና” አልሁ። 3 እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ራራ፤ “ይህ አይሆንም፤” ይላል እግዚአብሔር። ራእይ ስለ እሳት 4 ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም ጌታ እግዚአብሔር ለመፍረድ በቃሉ እሳትን ጠራ፤ እርስዋም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። 5 እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብን ማን ያነሣዋል? ጥቂት ነውና” አልሁ። 6 እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ራራ፤ “ይህ ደግሞ አይሆንም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ነቢዩ ስለ ቱንቢ ያየው ራእይ 7 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም አንድ ሰው በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር፤ በእጁም ቱንቢ ነበር። 8 እግዚአብሔርም፥ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም፥ “ቱንቢ ነው” አልሁ። ጌታም፥ “እነሆ! በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ ይቅር አልላቸውም። 9 መሳቂያ የሆኑ የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ” አለ። አሞጽና አሜስያስ 10 የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም ልኮ፥ “አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል ዐምፆብሃል፤ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም” አለ። 11 አሞጽ፥ “ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፤ እስራኤልም ከሀገሩ ተማርኮ ይሄዳል” ብሎአልና። 12 አሜስያስም አሞጽን፥ “ባለ ራእዩ ሆይ! ሂድ፤ ወደ ይሁዳ ምድር ሽሽ፤ በዚያም ተቀመጥ፥ በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ 13 ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትንቢት አትናገር” አለው። 14 አሞጽም መልሶ አሜስያስን አለው፥ “እኔ ላም ጠባቂና በለስ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ 15 እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፤ እግዚአብሔርም፦ ሂድ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ። 16 አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ አንተ፦ በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ የያዕቆብንም ቤት አትዘብዝባቸው ብለሃል። 17 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ አመንዝራ ትሆናለች፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ምድርህም በገመድ ትከፈላለች፤ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፤ እስራኤልም ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።” |