1 ነገሥት 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የእግዚአብሔርም ቃል ስለ ባኦስ እንዲህ ብሎ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ። 2 “እኔ ከመሬት አንሥቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌሃለሁ፤ አንተ ግን በከንቱ ጣዖታቸው ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቤን እስራኤልን በአሳታቸው በኢዮርብዓም መንገድ ሄድህ፤ 3 ስለዚህም፥ እነሆ፥ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርጋለሁ። 4 ከባኦስም ወገን በከተማዪቱ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሚሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።” 5 የቀረውም የባኦስ ነገር፥ የሠራውም ሁሉ፥ ኀይሉም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። 6 ባኦስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቴርሳም ተቀበረ፤ ልጁም ኤላ በአሳ በሃያ ስድስተኛው ዓመተ መንግሥት በፋንታው ነገሠ። 7 በእጁም ሥራ ያስቈጣው ዘንድ፥ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ስላደረገው ክፋት ሁሉ እርሱንም ስለ ገደለው፥ የእግዚአብሔር ቃል በባኦስና በቤቱ ላይ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢዩ መጣ። 8 የባኦስም ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ በቴርሳ ሁለት ዓመት ነገሠ። 9 የእኩሌቶቹ ፈረሶች አለቃ ዘምሪም አሽከሮቹን ሁሉ ሰብስቦ ዐመፀ፤ ኤላም በቴርሳ ነበረ፤ በቴርሳም በነበረው በመጋቢው በአሳ ቤት ይሰክር ነበር። 10 በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ ገብቶ ወጋና ገደለው፤ በፋንታውም ነገሠ። 11 ከነገሠና በዙፋኑም ከተቀመጠ በኋላ፥ የባኦስን ቤት ሁሉ አጠፋ፤ አንድ ወንድ እንኳ አላስቀረለትም። 12 በነቢዩ በኢዩ አፍ በባኦስ ቤት ላይ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ 13 ባኦስና ልጁ ኤላ ስለ ሠሩት ኀጢአት ሁሉ፥ በርኵሰታቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ስለ አሳቱበት ኀጢአት፥ ዘምሪ የባኦስን ቤት ሁሉ እንዲሁ አጠፋ። 14 የቀረውም የኤላ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። 15 በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሃያ ዘጠነኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሰባት ቀን ነገሠ። የእስራኤል ሠራዊት ግን በፍልስጥኤም ሀገር በገባቶን ሰፍረው ነበር። 16 በሰፈር ያሉ ሕዝቡም “ዘምሪ ከድቶ ኤላን ገደለው፥ በፋንታውም ነገሠ” ሲሉ ሰሙ። እስራኤልም ሁሉ በዚያ ቀን በሰፈሩ ውስጥ የሠራዊቱን አለቃ ዘንበሪን አነገሡ። 17 ዘንበሪም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከገባቶን ወጥተው ቴርሳን ከበቡ። በእርስዋም ተቀመጡ። 18 ዘምሪም ከተማዪቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ገባ፤ የንጉሡንም ቤት በራሱ ላይ በእሳት አቃጠለ፤ ሞተም። 19 ስላደረገውም ኀጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት ኀጢአት፥ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርጎአልና፥ በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓምም መንገድ ሄዶአልና ሞተ። 20 የቀረውም የዘምሪ ነገር፥ ያደረገውም ዐመፅ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። 21 በዚያም ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት ተከፈለ፤ የሕዝቡም እኩሌታ የጎናትን ልጅ ታምኒን ያነግሡት ዘንድ ተከተሉት፤ እኩሌቶችም ዘንበሪን ተከተሉ። 22 ዘንበሪንም የተከተሉ ሕዝብ የጎናት ልጅ ታምኒን የተከተሉትን ሕዝብ ድል አደረጉአቸው፤ ታምኒም ሞተ፤ ወንድሙም ኢዮራም በዚያው ዘመን ሞተ፤ ከታምኒ በኋላ ዘንበሪ ነገሠ። 23 በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሠላሳ አንደኛው ዓመተ መንግሥት ዘንበሪ በእስራኤል ላይ ዐሥራ ሁለት ዓመት ነገሠ። በቴርሳም ስድስት ዓመት ነገሠ። 24 ዘንበሪም ከዚያች ተራራ ባለቤት ከሴሜር በሁለት መክሊት ብር የሳምሮንን ተራራ ገዛ፤ በተራራውም ላይ ከተማ ሠራ፤ የሠራትንም ከተማ በተራራው ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራት። 25 ዘንበሪም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ከእርሱም አስቀድሞ ከነበሩት ይልቅ እጅግ ከፋ። 26 በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሁሉ በርኩስነታቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ባሳተበት ኀጢአት ሄደ። 27 የቀረውም ዘንበሪ ያደረገው ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። 28 ዘንበሪም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት፤ ልጁም አክአብ በፋንታው ነገሠ። 28 ‘ሀ’ ዘንበሪም ዐሥራ አንድ ዓመት ሲሆነው የአሳ ልጅ ኢዮሳፍጥ ነገሠ። በነገሠም ጊዜ ሠላሳ አምስት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ አምስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ጋዙባ የምትባል የሴላህ ልጅ ነበረች። 28 ‘ለ’ በአባቱም በአሳ መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ጽድቅን ያደርግ ዘንድ ከእርስዋ ፈቀቅ አላለም። በተራሮች የነበሩትንም አማልክት አላስወገደም፤ ሕዝቡም በተራሮቹ ይሠዉላቸውና ያጥኑላቸው ነበረ። 28 ‘ሐ’ ኢዮሳፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የሠራው፥ የተዋጋውና ያደረገው ኀይል ሁሉ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ ነው። 28 ‘መ’ በአባቱም በአሳ ዘመን የነበረውን ርኵሰት ሁሉ ከምድር አስወገደ። በኤዶምም ንጉሥ አልነበረም። 28 ‘ሠ’ ንጉሥ ኢዮሳፍጥም ወርቅና ብርን ሊያመጡለት ወደ አፌር ይልክ ዘንድ በተርሴስ መርከብ አሠራ፤ በጋስዮንጋቤር የነበረችው መርከብ ተሰብራለችና አልሄደችም። 28 ‘ረ’ የእስራኤልም ንጉሥ አካዝያስ ኢዮሳፍጥን፥ “አገልጋዮችህንና አገልጋዮቼን በመርከብ እንላክ” አለው። ኢዮሳፍጥም እንቢ አለ። 28 ‘ሰ’ ኢዮሳፍጥም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ። በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንደ ነገሠ 29 በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሳፍጥ በሁለተኛው ዓመት የዘንበሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ሃያ ሁለት ዓመት ነገሠ። 30 አክዓብም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 31 በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም ኀጢአት መሄድ አልበቃውም፤ የሲዶናውያንንም ንጉሥ የኤያትባሔልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፤ ሄዶም በዓልን አመለከ ሰገደለትም። 32 በሰማርያም በሠራው በበዓል ቤት ውስጥ ለበዓል መሠዊያን ሠራ። 33 አክዓብም የማምለኪያ ዐፀድን አሠራ፤ አክዓብም ሰውነቱ እንድትጠፋ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያስቈጣውን ነገር አበዛ። 34 በእርሱም ዘመን የቤቴል ሰው አኪያል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ ቃል እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ በበኵር ልጁ በአቢሮን መሠረቷን አደረገ፥ በታናሹ ልጁም በዜጉብ በሮችዋን አቆመ። |