1 ነገሥት 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰሎሞን ከእግዚአብሔር እንደ ራቀ 1 ንጉሡም ሰሎሞን ሴቶችን ይወድ ነበር፥ ከባዕዳን ሕዝብም የፈርዖንን ልጅ፥ ሞዓባውያትንና አሞናውያትን፥ ሶርያውያትንና ሲዶናውያትን፥ ኤዶማውያትንና አሞሬዎናውያትንም፥ ኬጤዎናውያትንም፦ ሚስቶችን አገባ። 2 እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች፥ “አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን እንዳይመልሱ ወደ እነርሱ አትግቡ፥ እነርሱም ወደ እናንተ አይግቡ” ካላቸው ከአሕዝብ አገባ፤ ሰሎሞን ግን እነርሱን ተከተለ፤ ወደዳቸውም። 3 ለእርሱም ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት። 4 ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ልቡ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር አልነበረም። ከባዕድ ያገባቸው ሚስቶቹም ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን መለሱት። 5 ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስጠራጢስን የአሞናውያንንም ርኵሰት ኮሞስን ተከተለ። 6 ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን አልተከተለውም። 7 ያንጊዜም ሰሎሞን ለሞአብ ርኵሰት ለኮሞስ፥ ለአሞን ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም አንጻር በአለው ተራራ ላይ መስገጃን ሠራ። 8 ሰሎሞንም ልዩ ከሆኑ ከአሕዝብ ለአገባቸው ሚስቶቹ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ ለጣዖቶቻቸውም መሥዋዕትን ሠዋ፤ ዕጣንም አጠነ። 9 ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡናውን መልሶአልና እግዚአብሔር በሰሎሞን ላይ ቍጣን ተቈጣ። 10 ስለዚህም ነገር ወደ ባዕድ አምልኮት እንዳይሄድ፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ሁሉ ይጠብቅና ያደርግ ዘንድ አዘዘው፤ ልቡናው ግን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልሆነም። 11 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው፥ “ይህን ሠርተሃልና፥ ያዘዝሁህንም ትእዛዜንና ሕጌን አልጠብቅህምና መንግሥትህን ከአንተ ከፍዬ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ። 12 ነገር ግን ከልጅህ እጅ እከፍለዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም። 13 ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ሀገሬ ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልከፍልም።” 14 እግዚአብሔርም ኤዶማዊው አዴርን ከረምማቴር ወገን የኤልያዳሔ ልጅ ኤስሮምን የሲባ ንጉሥ ጌታውን አድረዓዛርን ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣ። ሰዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። የዓመፁም አበጋዝ እርሱ ነበር። ደማስቆንም እጅ አደረጋት። በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ በእስራኤል ላይ ጠላት ሆነ። ኤዶማዊው አዴርም ከኤዶምያስ ነገሥታት ዘር ነበር። በሰሎሞን ላይ ጠላት እንደ ተነሣበት 15 ዳዊትም ኤዶምያስን ባጠፋ ጊዜ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ ተወግተው የሞቱትን ሊቀብር በወጣ ጊዜ፥ የኤዶምያስንም ወንድ ሁሉ በገደለ ጊዜ፥ 16 ኢዮአብና እስራኤልም ሁሉ የኤዶምያስን ወንድ ሁሉ እስኪገድሉ ድረስ ስድስት ወር በዚያ ተቀምጠው ነበር። 17 አዴር፥ ከእርሱም ጋር ከኤዶምያስ ሰዎች የሆኑ የአባቱ አገልጋዮች ሁሉ ኰበለሉ፤ ወደ ግብፅም ገቡ። አዴር ግን ገና ሕፃን ነበር። 18 ከምድያምም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ ከእነርሱም ጋር ከፋራን ሰዎችን ወሰዱ፤ ወደ ግብፅም መጡ፤ ወደ ግብፅም ንጉሥ ወደ ፈርዖን ሄዱ፤ አዴርም ወደ ፈርዖን ገባ። እርሱም ቤት ሰጥቶ ቀለብ ዳረገው። 19 አዴርም በፈርዖን ፊት እጅግ ባለምዋል ሆነ። የሚስቱንም የቴቄምናስን ታላቅ እኅት ሚስት አጋባው። 20 የቴቄምናስ እኅት ወንድ ልጅ ጌንባትን ለአዴር ወለደችለት፤ ቴቄምናስም በፈርዖን ልጆች መካከል አሳደገችው፤ ጌንባትም በፈርዖን ልጆች መካከል ነበረ። 21 አዴርም በግብፅ ሳለ ዳዊት እንደ አባቶቹ እንዳንቀላፋ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ አዴር ፈርዖንን፥ “ወደ ሀገሬ እሄድ ዘንድ አሰናብተኝ” አለው። 22 ፈርዖንም፥ “እነሆ፥ ከእኔ ዘንድ ወደ ሀገርህ መሄድ የፈለግህ ምን አጥተህ ነው?” አለው። አዴርም፥ “አንዳች አላጣሁም፤ ነገር ግን ልሂድ” ብሎ መለሰ። አዴርም ወደ ሀገሩ ተመለሰ። 23 እግዚአብሔርም ደግሞ ከጌታው ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር የኰበለለውን የኤልያዳን ልጅ ሬዞንን ጠላት አድርጎ አስነሣበት። 24 ዳዊትም የሲባን ሰዎች በገደለ ጊዜ ሬዞን ሰዎችን ሰብስቦ የጭፍራ አለቃ ሆነ፤ ወደ ደማስቆም ሄዱ፥ በዚያም ተቀመጡ፤ በደማስቆም ላይ አነገሡት። 25 በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ የእስራኤል ጠላት ነበረ። አዴርም ያደረጋት ክፋት ይህች ናት፤ እስራኤልን አስጨነቀ በኤዶምያስም ነገሠ። ኢዮርብዓም እንደሚነግሥ ትንቢት እንደ ተነገረለት 26 ከሳሪራ ሀገር የሆነ የኤፍሬማዊው የናባጥና ሳሩሃ የተባለች የመበለት ልጅ ኢዮርብዓም የሰሎሞን አገልጋይ ነበረ። 27 እርሱም ያደረገው ይህ ነው በንጉሡ በሰሎሞን ላይ እጁን አነሣ፤ ሰሎሞንም በዳርቻ ያለ ቅጥርንና የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጥር ሠርቶ ጨረሰ። 28 ኢዮርብዓምም ጽኑዕ ኀያል ሰው ነበረ፤ ሰሎሞንም ጐልማሳው ኢዮርብዓም በሥራ የጸና መሆኑን ባየ ጊዜ በዮሴፍ ነገድ ሥራ ሁሉ ላይ ሾመው። 29 ከዚህ በኋላም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ሴሎናዊው ነቢዩ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ ከመንገድም ገለል አደረገው፤ አኪያም አዲስ ልብስ ለብሶ ነበር። ሁለቱም በሜዳ ነበሩ። 30 አኪያም የለበሰውን አዲስ ልብስ ይዞ ከዐሥራ ሁለት ቀደደው። 31 ኢዮርብዓምንም አለው፥ “ዐሥር ቅዳጅ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ ከሰሎሞን እጅ መንግሥቱን እለያታለሁ፤ ዐሥሩንም ነገዶች እሰጥሃለሁ። 32 ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከእስራኤልም ሀገሮች ሁሉ ስለ መረጥኋት ከተማ ስለ ኢየሩሳሌም ግን ሁለት ነገድ ይቀሩለታል፤ 33 ትቶኛልና፥ ለሲዶናውያንም ርኵሰት ለአስጠራጢስ፥ ለሞአብም አምላክ ለኮሞስ፥ ለአሞንም ልጆች አምላክ ለሞሎክ ሰግዶአልና፥ አባቱም ዳዊት እንዳደረገ በፊቴ ቅን ነገርን ያደርግ ዘንድ በመንገዶቼ አልሄደምና። 34 መንግሥቱንም ሁሉ ከእጁ አልወስድም፤ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ስለ ጠበቀው ስለ መረጥሁት ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ግን በዕድሜው ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ። 35 መንግሥቱንም ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፤ ለአንተም ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ። 36 ስሜንም ባኖርሁባት በዚያች በመረጥኋት ከተማ በኢየሩሳሌም ለባሪያዬ ለዳዊት በፊቴ ሁልጊዜ መብራት ይሆንለት ዘንድ ለልጁ ሁለት ነገድን እሰጠዋለሁ። 37 አንተንም እወስድሃለሁ፤ ነፍስህም በወደደችው ሁሉ ላይ አነግሥሃለሁ፤ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ትሆናለህ። 38 ባሪያዬም ዳዊት እንዳደረገ፥ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትሰማ፥ በመንገዴም ብትሄድ፥ በፊቴም የቀናውን ብታደርግ፥ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ብትጠብቅ፥ ከአንተ ጋር እኖራለሁ፤ ለዳዊትም እንደ ሠራሁለት የታመነ ቤትን እሠራልሃለሁ፤ እስራኤልንም ለአንተ እሰጥሃለሁ። 39 ስለዚህም የዳዊትን ዘር አስጨንቃለሁ፤ ነገር ግን በዘመን ሁሉ አይደለም።” 40 ሰሎሞንም ኢዮርብዓምን ሊገድለው ወደደ፤ ኢዮርብዓምም ተነሥቶ ወደ ግብፅ ሀገር፥ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሱስቀም ኰብልሎ ሄደ፥ ሰሎሞንም እስኪሞት ድረስ በግብፅ ተቀመጠ። የሰሎሞን ሞትና የሮብዐም መንገሥ ( 2ዜ.መ. 9፥29-31 ) 41 የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ ጥበቡም ሁሉ፥ እነሆ፥ በሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 42 ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። 43 ሰሎሞንም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በፋንታው ነገሠ። |