Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 88 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 88
ማሕሌት፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር፤ ለመዘምራን አለቃ፤ በማኸላት ሌዓኖት የሚዘመር፤ የይዝራኤላዊው የኤማን ማስኪል።

1 አዳኜ የሆንህ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በቀንና በሌሊት በፊትህ እጮኻለሁ።

2 ጸሎቴ በፊትህ ትድረስ፤ ጆሮህንም ወደ ጩኸቴ አዘንብል።

3 ነፍሴ በመከራ ተሞልታለችና፤ ሕይወቴም ወደ ሲኦል ተቃርባለች።

4 ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋራ ተቈጠርሁ፤ ዐቅምም ዐጣሁ።

5 በሙታን መካከል እንደ ተጣሉ፣ ተገድለው በመቃብር ውስጥ እንደ ተጋደሙ፣ አንተ ከእንግዲህ እንደማታስባቸው፣ ከእጅህም ወጥተው እንደ ተወገዱ ሆንሁ።

6 በዐዘቅት ጥልቀት ውስጥ ጣልኸኝ፤ በጨለማ ጕድጓድ ውስጥ ከተትኸኝ።

7 የቍጣህ ክብደት በላዬ ዐርፏል፤ በማዕበልህም ሁሉ አጥለቅልቀኸኛል። ሴላ

8 የሚቀርቡኝ ባልንጀሮቼን ከእኔ አራቅህ፤ እንዲጸየፉኝም አደረግህ፤ ተከብቤአለሁ፤ ማምለጥም አልችልም፤

9 ዐይኖቼም በሐዘን ፈዘዙ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ዘወትር ወደ አንተ እጣራለሁ፤ እጆቼንም ወደ አንተ ዘረጋሁ።

10 ድንቅ ሥራህን ለሙታን ታሳያለህን? የሙታንስ መናፍስት ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? ሴላ

11 ምሕረትህ በመቃብር ውስጥ፣ ታማኝነትህስ እንጦርጦስ ይነገራልን?

12 ድንቅ ሥራህ በጨለማ ስፍራ፣ ጽድቅህስ በመረሳት ምድር ትታወቃለችን?

13 እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን ትረዳኝ ዘንድ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በጧትም ጸሎቴን በፊትህ አደርሳለሁ።

14 እግዚአብሔር ሆይ፤ ለምን ታርቀኛለህ? ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ?

15 እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ችግረኛና ለሞት የተቃረብሁ ነበርሁ፤ መዓትህ አሠቃየኝ፤ ግራም ተጋባሁ።

16 ቍጣህ በላዬ ላይ ተከነበለ፤ መዓትህም አጠፋኝ።

17 ቀኑን ሙሉ እንደ ጐርፍ ከበቡኝ፤ በአንድነትም ዙሪያዬን ዐጥረው ያዙኝ።

18 ወዳጄንና ባልንጀራዬን ከእኔ አራቅህ፤ ጓደኛዬ ጨለማ ብቻ ሆኖ ቀረ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos