Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 44 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 44
ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች ማስኪል።

1 አምላክ ሆይ፤ በጆሯችን ሰምተናል፤ አባቶቻችን በቀድሞ ዘመን፣ እነርሱ በነበሩበት ዘመን፣ ያደረግኸውን ነግረውናል።

2 ሕዝቦችን በእጅህ አሳድደህ አወጣሃቸው፤ አባቶቻችንን ግን ተከልሃቸው፤ ሕዝቦችን አደቀቅህ፤ አባቶቻችንን ግን ነጻ አወጣሃቸው።

3 ምድሪቱን የወረሱት በሰይፋቸው አልነበረም፤ ድልንም የተጐናጸፉት በክንዳቸው አይደለም፤ አንተ ወድደሃቸዋልና ቀኝ እጅህ፣ ክንድህና የፊትህ ብርሃን ይህን አደረገ።

4 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ንጉሤ ነህ፤ ያዕቆብም ድል እንዲያደርግ የወሰንህ አንተ ነህ።

5 በአንተ ጠላቶቻችን በመጡበት እንዲመለሱ እናደርጋለን፤ በስምህም ባላጋራዎቻችንን ከእግራችን በታች እንረግጣለን።

6 በቀስቴ አልተማመንም፤ ሰይፌም አያስጥለኝም።

7 አንተ ግን በጠላቶቻችን ላይ ድልን ትሰጠናለህ፤ ባላንጣዎቻችንንም ታሳፍራለህ።

8 ዘወትር በእግዚአብሔር እንመካለን፤ ስምህንም ለዘላለም እንወድሳለን። ሴላ

9 አሁን ግን እነሆ ትተኸናል፤ አሳፍረኸናልም፤ ከሰራዊታችንም ጋራ አትወጣም።

10 ከጠላት ፊት እንድናፈገፍግ አደረግኸን፤ ባላንጣዎቻችንም ዘረፉን።

11 እንደሚታረዱ በጎች አደረግኸን፤ በሕዝቦችም መካከል በተንኸን።

12 ሕዝብህን በርካሽ ዋጋ ሸጥኸው፤ ከሽያጩም ያገኘኸው ትርፍ የለም።

13 ለጎረቤቶቻችን ስድብ፣ በዙሪያችን ላሉትም መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን።

14 በሕዝቦች ዘንድ መተረቻ፣ በሰዎች መካከል በንቀት ራስ መነቅነቂያ አደረግኸን።

15 ውርደቴ ቀኑን ሙሉ በፊቴ ነው፤ ፊቴም ዕፍረትን ተከናንቧል።

16 ይህም ከሚዘልፍና ከሚያላግጥ ሰው ድምፅ የተነሣ፣ ከጠላትና ከተበቃይ ሁኔታ የተነሣ ነው።

17 አንተን ሳንረሳ፣ ለኪዳንህም ታማኝነታችንን ሳናጓድል፣ ይህ ሁሉ ደረሰብን።

18 ልባችን ወደ ኋላ አላለም፤ እግራችንም ከመንገድህ አልወጣም።

19 አንተ ግን ተኵላዎች በሚውሉበት ቦታ ሰባብረህ ጣልኸን፤ በሞት ጥላም ሸፈንኸን።

20 የአምላካችንን ስም ረስተን፣ እጃችንንም ወደ ባዕድ አምላክ ዘርግተን ቢሆን ኖሮ፣

21 እግዚአብሔር ይህን ማወቅ ይሳነዋልን? እርሱ ልብ የሰወረውን የሚረዳ ነውና።

22 ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጥረናል።

23 ጌታ ሆይ፤ ንቃ! ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፤ ለዘላለምም አትጣለን።

24 ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? መከራችንንና መጠቃታችንን ለምን ትረሳለህ?

25 ነፍሳችን ዐፈር ውስጥ ሰጥማለች፤ ሆዳችንም ከምድር ጋራ ተጣብቋል።

26 ተነሥና እርዳን! ስለ ምሕረትህ ስትል ተቤዠን።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos