መዝሙር 132 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 132 132፥8-10 ተጓ ምብ – 2ዜና 6፥41-42 መዝሙረ መዓርግ። 1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ዳዊትን፣ የታገሠውንም መከራ ሁሉ ዐስብ። 2 እርሱ ለእግዚአብሔር ማለ፤ ለያዕቆብም ኀያል አምላክ እንዲህ ሲል ተሳለ፤ 3 “ወደ ቤቴ አልገባም፤ ዐልጋዬም ላይ አልወጣም፤ 4 ለዐይኖቼ እንቅልፍን፣ ለሽፋሽፍቶቼም ሸለብታ አልሰጥም፤ 5 ለእግዚአብሔር ስፍራን፣ ለያዕቆብም ኀያል አምላክ ማደሪያን እስካገኝ ድረስ።” 6 እነሆ፤ በኤፍራታ ሰማነው፤ በቂርያትይዓሪም አገኘነው። 7 “ወደ ማደሪያው እንግባ፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንስገድ። 8 እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ፣ ከኀይልህ ታቦት ጋራ ወደ ማረፊያ ቦታህ ግባ። 9 ካህናትህ ጽድቅን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም እልል ይበሉ።” 10 ስለ ባሪያህ ስለ ዳዊት ስትል፣ የቀባኸውን ሰው አትተወው። 11 እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ፤ በማይታጠፍም ቃሉ እንዲህ አለ፤ “ከሆድህ ፍሬዎች አንዱን፣ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ። 12 ወንዶች ልጆችህ ኪዳኔን፣ የማስተምራቸውንም ምስክርነቴን ቢጠብቁ፣ ልጆቻቸው በዙፋንህ ላይ፣ ለዘላለም ይቀመጣሉ።” 13 እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና፣ ማደሪያውም ትሆን ዘንድ ወድዷልና እንዲህ አለ፤ 14 “ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ ፈልጌአታለሁና በርሷ እኖራለሁ። 15 እጅግ አትረፍርፌ እባርካታለሁ፤ ድኾቿን እንጀራ አጠግባለሁ። 16 ለካህናቷ ድነትን አለብሳለሁ፤ ቅዱሳኗም በደስታ ይዘምራሉ። 17 “በዚህም ለዳዊት ቀንድ አበቅላለሁ፤ ለቀባሁትም ሰው መብራት አዘጋጃለሁ። 18 ጠላቶቹን ኀፍረት አከናንባቸዋለሁ፤ እርሱ ግን በራሱ ላይ የደፋው ዘውድ ያበራል።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.