2 ነገሥት 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኢዩ ተቀብቶ በእስራኤል ላይ ነገሠ 1 ነቢዩ ኤልሳዕ ከነቢያት ማኅበር አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ወገብህን ታጥቀህ፣ ይህን የዘይት ማሰሮ በመያዝ በራሞት ወደምትገኘው ገለዓድ ሂድ። 2 በዚያም ስትደርስ የናሜሲን የልጅ ልጅ፣ የኢዮሣፍጥን ልጅ ኢዩን ፈልገው። ወደ እርሱም ቀርበህ ከጓደኞቹ ለብቻ ከነጠልኸው በኋላ፣ ወደ እልፍኝ አስገባው። 3 ከዚያም ማሰሮውን ይዘህ ዘይቱን በራሱ ላይ አፍስስና፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ እኔ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀባሁህ” ’ ብለህ ዐውጅ። ከዚያም በሩን ከፍተህ ሩጥ፤ ፈጽሞ አትዘግይ።” 4 ስለዚህ ጕልማሳው ነቢይ በራሞት ወደምትገኘው ገለዓድ ሄደ። 5 በዚያ እንደ ደረሰም፣ የሰራዊቱ ጦር መኰንኖች በአንድነት ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም “መኰንን ሆይ፤ ወደ አንተ ተልኬአለሁ” አለ። ኢዩም፣ “ለማንኛችን ነው?” ሲል ጠየቀ። እርሱም፣ “መኰንን ሆይ፤ ለአንተ ነው” ብሎ መለሰ። 6 ኢዩም ተነሥቶ ወደ ቤት ገባ፤ ከዚያም ነቢዩ ዘይቱን በኢዩ ላይ አፈሰሰና እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀብቼሃለሁ። 7 የአገልጋዮቼን የነቢያትን ደም እንዲሁም የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ደም ሁሉ ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ አንተ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ። 8 የአክዓብ ቤት በሙሉ ይጠፋል፤ ባሪያም ይሁን ተወላጅ፣ በእስራኤል የሚገኘውን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ሁሉ ከአክዓብ እቈርጣለሁ። 9 ከእንግዲህ የአክዓብን ቤት፣ እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፣ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ። 10 ኤልዛቤልን ግን በኢይዝራኤል ዕርሻ ውሾች ይበሏታል፤ የሚቀብራትም አይኖርም።’ ” ይህን ተናግሮም መዝጊያውን ከፍቶ ሮጠ። 11 ኢዩ ወጥቶ የጦር አለቆች ወደሆኑት ጓደኞቹ እንደ ደረሰ፣ ከመካከላቸው አንዱ “ሁሉም ነገር ሰላም ነው? ይህ እብድ ወደ አንተ የመጣው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢዩም “ሰውየውንም ሆነ የሚናገረውን እናንተም ታውቃላችሁ” ሲል መለሰ። 12 እነርሱም፣ “ይህማ ትክክል አይደለም፤ ይልቅስ እውነቱን ንገረን” አሉት። ኢዩም እንዲህ አለ፤ “እርሱ የነገረኝማ ይህ ነው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ንጉሥ እንድትሆን ቀብቼሃለሁ።’ ” 13 ከዚያ ሁሉም ቶሎ ብለው ልብሳቸውን እያወለቁ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፤ ከዚያም መለከት ነፍተው፣ “ኢዩ ነግሧል” አሉ። ኢዩ ኢዮራምንና አካዝያስን ገደለ 9፥21-29 ተጓ ምብ – 2ዜና 22፥7-9 14 ስለዚህ የናሜሲ የልጅ ልጅ፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ በኢዮራም ላይ አሤረ። በዚህ ጊዜ ኢዮራምና እስራኤል ሁሉ በራሞት የምትገኘውን ገለዓድን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጥቃት ለማዳን ይጠብቁ ነበር። 15 ንጉሥ ኢዮራም ግን የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን ጦርነት በገጠመው ጊዜ፣ ሶርያውያን ካደረሱበት ቍስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም፣ “እንግዲህ ሐሳባችሁ እንዲህ ከሆነ፣ ይህን ነገር ወደ ኢይዝራኤል ሄዶ እንዳይናገር፣ ማንም ሰው ከዚህች ከተማ ሾልኮ እንዳይወጣ ጠብቁ” አለ። 16 ከዚያም ኢዩ በሠረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ ይህን ያደረገውም ኢዮራም በዚያ ስለ ተኛና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም እርሱን ለመጠየቅ ወደዚያው ስለ ወረደ ነው። 17 በኢይዝራኤል ግንብ ማማ ላይ የቆመው ጠባቂ የኢዩ ወታደሮች መቅረባቸውን አይቶ፣ “ኧረ ወታደሮች መጡ” በማለት ጮኾ ተናገረ። ኢዮራምም፣ “አንድ ፈረሰኛ ተጠርቶ፤ እንዲገናኛቸው ላኩትና፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሎ ይጠይቅ” ሲል አዘዘ። 18 ፈረሰኛውም ኢዩን ለመገናኘት ጋልቦ ሄደና፣ “ንጉሡ፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሏል” አለው። ኢዩም፣ “ስለ ሰላም መጨነቅ የአንተ ጕዳይ አይደለም! ይልቅስ ወደ ኋላ ዕለፍና ተከተለኝ” አለው። ጠባቂውም፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሷል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ብሎ አሳወቀ። 19 ስለዚህ ንጉሡ ሌላ ፈረሰኛ ላከ፤ ወደ እነርሱ ዘንድ እንደ ደረሰም፣ “ንጉሡ፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ይላል” አለው። ኢዩም “ስለ ሰላም መጨነቅ የአንተ ጕዳይ አይደለም! ይልቅስ ወደ ኋላ ዕለፍና ተከተለኝ” አለው። 20 ጠባቂው፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሷል፤ ነገር ግን ይህም ተመልሶ አልመጣም፤ የወታደሮቹ መሪ ሠረገላ አነዳዱ ልክ እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ አነዳድ ነው፤ ሲነዳም እንደ እብድ ነው” ሲል አሳወቀ። 21 ኢዮራምም፣ “ሠረገላዬን አዘጋጁ” ብሎ አዘዘ። ሠረገላው እንደ ተዘጋጀም፣ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራምና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ በየሠረገሎቻቸው ሆነው ኢዩን ለመገናኘት ሄዱ፤ የኢይዝራኤላዊው የናቡቴ ርስት በነበረው ዕርሻ ላይም ተገናኙት። 22 ኢዮራምም ኢዩን ገና ሲያየው፣ “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀው። ኢዩም፣ “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” ሲል መለሰ። 23 ኢዮራምም ሠረገላውን አዙሮ በመሸሽ፣ “አካዝያስ ሆይ፤ ይህ ክዳት ነው!” አለ። 24 ከዚያም ኢዩ ቀስቱን በማስፈንጠር ኢዮራምን በትከሻና ትከሻው መካከል ወጋው፤ ፍላጻውም ዘልቆ ልቡን ስለ ወጋው፣ ሠረገላው ውስጥ ዘፍ ብሎ ወደቀ። 25 ኢዩም የሠረገላ ኀላፊውን ቢድቃርን እንዲህ አለው፤ “አንሣውና በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ ዕርሻ ላይ ጣለው፤ አንተና እኔ አባቱን አክዓብን በየሠረገሎቻችን ሆነን ተከትለነው ስንሄድ፣ እግዚአብሔር ይህን ትንቢት እንዲህ ሲል እንደ ተናገረበት አስታውስ፤ 26 ‘ትናንት የናቡቴንና የልጆቹን ደም አይቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር’ ይህንም በዚሁ ዕርሻ ላይ በርግጥ አንተው እንድትከፍል አደርግሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ አሁንም በእግዚአብሔር ቃል በተነገረው መሠረት አንሣውና በዚሁ ዕርሻ ውስጥ ጣለው።” 27 የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ይህን ሲያይ፣ ወደ ቤት ሀጋን በሚያወጣው መንገድ ሸሸ፤ ኢዩም እያሳደደ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እርሱንም ግደሉት!” አለ። እነርሱም በይብለዓም ከተማ አጠገብ በጉር ዐቀበት መንገድ ላይ በሠረገላው ውስጥ እንዳለ አቈሰሉት፤ እርሱ ግን ወደ መጊዶ ሸሽቶ፤ እዚያው ሞተ። 28 አገልጋዮቹም በሠረገላ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋራ በመቃብሩ ቀበሩት። 29 አካዝያስ በይሁዳ የነገሠው፣ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር። ኤልዛቤል ተገደለች 30 ከዚያም ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤ ኤልዛቤልም ይህን በሰማች ጊዜ ዐይኗን ተኳኵላ፣ ጠጕሯንም አሰማምራ በመስኮት ትመለከት ነበር። 31 ኢዩ የቅጥሩን በር ዐልፎ ሲገባ፣ “ጌታህን የገደልህ አንተ ዘምሪ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው። 32 ቀና ብሎ ወደ መስኮቱ ተመለከተና፣ “ማነህ አንተ? ማነው የሚተባበረኝ” ሲል ጮኾ ተጣራ። ሁለት ሦስት ጃንደረቦችም ቍልቍል ወደ እርሱ ተመለከቱ፤ 33 ኢዩም፣ “ወደ ታች ወርውሯት!” አለ፤ እነርሱም ወረወሯት፤ ፈረሶቹ ሲረጋግጧትም ደሟ በግንቡና በፈረሶቹ ላይ ተረጨ። 34 ኢዩም ገብቶ በላ፤ ጠጣም። ከዚያም፣ “ይህች የተረገመችን ሴት ተመልከቷት፤ ምንም ቢሆን የንጉሥ ልጅ ናትና በሚገባ ቅበሯት” አለ። 35 ሊቀብሯት ሲወጡ ግን ከራስ ቅሏ፣ ከእግሯና ከእጇ በቀር ሌላ ያገኙት አልነበረም። 36 ተመልሰውም ይህን ሲነግሩት፣ ኢዩ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ለባሪያው ለቴስብያዊው ለኤልያስ፣ በኢይዝራኤል ምድር ዕርሻ ውስጥ ውሾች የኤልዛቤልን ሥጋ ይበሉታል፤ 37 ሥጋዋም በኢይዝራኤል ምድር ዕርሻ ውስጥ እንደ ፍግ ስለሚሆን፣ ማንም ሰው፣ ‘ይህች ኤልዛቤል ናት’ ሊል አይችልም ብሎ የተናገረው ቃል ይህ ነው።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.