Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ምሳሌ 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 መልካም ስም ከብዙ ሃብት ይሻላል፤ በሰው ዘንድ መወደድም ከብር ወይም ከወርቅ ይበልጣል።

2 ሀብታምንም ሆነ ድኻን የፈጠራቸው እግዚአብሔር ስለ ሆነ ሁለቱም በዚህ አንድ ናቸው።

3 ብልኅ ሰው አደጋ ሲመጣ አይቶ ይሸሸጋል። ማስተዋል የጐደለው ሰው ግን ሰተት ብሎ ወደ መከራ በመግባት ይጐዳል።

4 እግዚአብሔርን መፍራትና ትሑት መሆን ሀብት፥ ክብርና ሕይወትን ያስገኛል።

5 በክፉዎች መንገድ ላይ እሾኽና ወጥመድ አለ፤ ራሱን የሚጠብቅ ግን ከእነርሱ ይርቃል።

6 ልጅን እንዴት መኖር እንደሚገባው ብታስተምረው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።

7 ድኻ የሀብታም ሰው አገልጋይ ነው፤ ገንዘብ የሚበደር የአበዳሪው ባሪያ ነው።

8 ኃጢአትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፤ ቊጣውም የትም አያደርሰውም።

9 ምግቡን ከድኾች ጋር ስለሚካፈል ለጋሥ ሰው የተባረከ ይሆናል።

10 ፌዘኛን ሰው ብታስወጣ ጠብ ይቆማል፤ ጠብና ስድብም አይኖሩም።

11 የልብ ንጽሕናንና መልካም ንግግርን የሚወድ ሰው በንጉሥ ዘንድ የተወደደ ይሆናል።

12 የእግዚአብሔር ዐይኖች ዕውቀትን ይጠብቃሉ፤ እምነት የሌላቸውን ሰዎች ዕቅድ ግን ያስወግዳል።

13 ሰነፍ ሰው “ውጪ አንበሳ አለ፤ ብወጣ ይገድለኛል” ብሎ ይከራከራል። “አንበሳ ያገኘኛል” በማለት ከቤቱ አይወጣም።

14 የአመንዝራ ሴት አፍ እንደ ጥልቅ ጒድጓድ ነው። እግዚአብሔር የጠላቸው ሰዎችም ተይዘው ይወድቁበታል።

15 በልጅ ልብ ውስጥ ሞኝነት አለ፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያስወግደዋል።

16 ለሀብታሞች ስጦታ የሚሰጥ፥ ወይም ሀብት ለማግኘት ብሎ ድኾችን የሚጨቊን ሰው ይደኸያል።


ሠላሳ የጥበብ ምክሮች

17 ጠቢባን ሰዎች የተናገሩትን ሳስተምርህ አድምጥ፤ ከእነርሱ የምታገኘውን ትምህርት አጥና፤

18 ዘወትር ብታስታውሳቸውና ብትጠቀምባቸው ደስ ይሉሃል፤

19 እነርሱንም የማስተላልፍልህ እምነትህ በእግዚአብሔር እንዲሆን ብዬ ነው።

20 እነሆ ሠላሳ መመሪያዎችን ጽፌልሃለሁ፤ እነርሱ ዕውቀትና መልካም ምክር የሚገኙባቸው ናቸው፤

21 እውነት ምን እንደ ሆነም ያስተምሩሃል፤ “እውነትን ፈልገህ አቅርብ” ተብለህ ብትጠየቅም ትክክለኛውን መልስ ትሰጣለህ።


-1-

22 ምንም ስለሌላቸው፥ ድኾችን አትበዝብዝ፤ የተጨቈኑትንም ሰዎች በፍርድ ሸንጎ አታጒላላ፤

23 ይኸውም እግዚአብሔር ስለሚከራከርላቸውና የሚያስጨንቁአቸውንም ስለሚያስጨንቅ ነው።


-2-

24 ከንዴተኛና ከቊጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፤

25 የእርሱን ጠባይ ከተማርክ አትላቀቅም።


-3-

26 የሌላ ሰው ዕዳ ለመክፈል ዋስ አትሁን፤

27 መክፈል ባትችል የምትተኛበት አልጋ እንኳ ሳይቀር ያለህ ንብረት ሁሉ ይወስድብሃል።


-4-

28 የቀድሞ አባቶችህ ያኖሩትን የወሰን ምልክት አትለውጥ።


-5-

29 በሥራው የሠለጠነ ሰው ታያለህን? እንደዚህ ያለ ሰው በተራ ሰው ፊት ሳይሆን በነገሥታት ፊት ለአገልግሎት ይቆማል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos