Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 36 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ባሮክ የተጠቀለለውን ብራና ማንበቡ

1 የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ በአራተኛው ዓመት እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤

2 “እኔ እግዚአብሔር አንተን ማናገር ከጀመርኩበት ማለትም ኢዮስያስ ከነገሠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስለ እስራኤል፥ ስለ ይሁዳ ሕዝብና ስለ ሌሎችም ሕዝቦች ሁሉ የነገርኩህን ቃል ሁሉ በብራና ጻፈው፤

3 የይሁዳ ሕዝብ በእነርሱ ላይ ላመጣ ያቀድኩትን ጥፋት በሚሰሙበት ጊዜ ምናልባት ከክፉ ሥራቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እላለሁ።”

4 ስለዚህም የኔሪያን ልጅ ባሮክን ጠርቼ እግዚአብሔር የነገረኝን ቃል ሁሉ አንድ በአንድ እየነገርኩት በሚጠቀለል ብራና ጻፈው፤

5 ከዚህም በኋላ ለባሮክ የሚከተለውን መመሪያ ሰጠሁት፦ “ከእንግዲህ ወዲህ ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት አይፈቀድልኝም፤

6 ነገር ግን በሚቀጥለው ጊዜ ሕዝቡ በመጾም ላይ ሳሉ አንተ ወደዚያ እንድትሄድ እፈልጋለሁ፤ እግዚአብሔር ለእኔ የነገረኝን ቃል ሁሉ አንድ በአንድ እየነገርኩህ በሚጠቀለል ብራና ላይ የጻፍከውን ሁሉ ድምፅህን ከፍ አድርገህ አንብብላቸው፤ ከገጠር ከተሞቻቸው የመጡ የይሁዳ ሕዝብ ጭምር ሁሉም በሚሰሙበት ቦታ ይህን አድርግ፤

7 እግዚአብሔር አስፈሪ በሆነው ቊጣና መዓቱ ሕዝቡን እንደሚቀጣ የተናገረ በመሆኑ ምናልባት በመጸጸት ከክፉ ሥራቸው ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ይለምኑት ይሆናል።”

8 ስለዚህም ባሮክ ልክ እኔ እንደ ነገርኩት በቤተ መቅደስ የእግዚአብሔርን ቃል አነበበ።

9 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር የኢየሩሳሌም ሕዝብና ከይሁዳ ከተሞች የመጡት ሕዝብ ከእግዚአብሔር ምሕረትን ለማግኘት የጾም ጊዜ አወጁ።

10 ሕዝቡም ለማዳመጥ በሚችልበት ሁኔታ ባሮክ እኔ የነገርኩትን በብራና ጽፎት የነበረውን ቃል ሁሉ አነበበላቸው። በቤተ መቅደስ ውስጥ ይህን ያደረገው በጸሐፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ክፍል በኩል ዘልቆ ነበር፤ ክፍሉም የሚገኘው ወደ ቤተ መቅደስ ከሚያስገባው አዲስ የቅጽር በር አጠገብ በላይኛው አደባባይ በኩል አለፍ ብሎ ነበር።


በተጠቀለለ ብራና የተጻፈው ቃል ለባለሥልጣኖች እንደ ተነበበላቸው

11 የሳፋን የልጅ ልጅ የነበረው የገማርያ ልጅ ሚክያስ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ሁሉ ባሮክ ከብራናው ሲያነብ ሰማ።

12 እርሱም በቤተ መንግሥት ወደሚገኘው ባለሥልጣኖች ወደሚገኙበት ወደ ጸሐፊው ክፍል ሄደ፤ ጸሐፊው ኤሊሻማዕ፥ የሸማዕያ ልጅ ደላያ፥ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፥ የሳፋን ልጅ ገማርያ፥ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ ሌሎችም ባለ ሥልጣኖች እዚያ ተቀምጠው ነበር።

13 ሚክያስም ባሮክ ለሕዝቡ ሲያነብላቸው የሰማውን ቃል ሁሉ ነገራቸው፤

14 ከዚህ በኋላ ባለ ሥልጣኖቹ ሁሉ ባሮክ ለሕዝቡ ያነበበውን የብራና ጥቅል ይዞ እንዲመጣ ይነግረው ዘንድ ይሁዲን ላኩ፤ (ይሁዲ የነታንያ ልጅ ሲሆን፥ ነታንያ የሸሌምያ ልጅ፥ ሸሌምያም የኩሺ ልጅ ነው፤) ባሮክም የብራናውን ጥቅል ይዞ ወደ እነርሱ መጣ፤

15 እነርሱም “በል ተቀመጥና ጽሑፉን አንብብልን!” አሉት፤ ባሮክም እንደታዘዘው አደረገ።

16 አንብቦ ከጨረሰም በኋላ ከመደንገጣቸው የተነሣ እርስ በርሳቸው ተያይተው ባሮክን “ይህን ጉዳይ ለንጉሡ ማስታወቅ አለብን” አሉት፤

17 ከዚያ በኋላ “ይህን ነገር እንዴት እንደ ጻፍከው ንገረን፤ ይህን የጻፍከው ኤርምያስ በቃል እየነገረህ ነውን?” ሲሉ ጠየቁት።

18 ባሮክም “በእርግጥ ቃሉን አንድ በአንድ የነገረኝ ኤርምያስ ነው፤ እኔም በዚህ ብራና ላይ በቀለም ጻፍኩት” አላቸው።

19 እነርሱም “አንተና ኤርምያስ ወደ አንድ ስፍራ ሄዳችሁ መደበቅ አለባችሁ፤ ያላችሁበትንም ቦታ ማንም ሰው አይወቅ” አሉት።


ንጉሡ የብራናውን ጥቅል ማቃጠሉ

20 ባለ ሥልጣኖቹም የብራናውን ጥቅል በጸሐፊው በኤሊሻማዕ ክፍል አኖሩት፤ ወደ ንጉሥም አደባባይ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ አሳወቁት፤

21 ንጉሡም የብራናውን ጥቅል ያመጣለት ዘንድ ይሁዲን አዘዘው፤ እርሱም ብራናውን ከኤሊሻማ ክፍል ወስዶ ለንጉሡና በዙሪያው ቆመው ለነበሩት ባለ ሥልጣኖች ሁሉ አነበበላቸው።

22 በዘጠነኛው ወር ወራቱም ክረምት ስለ ነበረ ንጉሡ የክረምትን ወራት በሚያሳልፍበት ቤተ መንግሥት እሳት በሚነድበት ምድጃ ፊት ለፊት ተቀምጦ ነበር፤

23 ይሁዲም ሦስት ወይም አራት ዐምድ ያኽል አንብቦ በጨረሰ ቊጥር ንጉሡ የተነበበለትን ብራና በመቊረጫ ቈራርጦ እሳት ውስጥ ይጥለው ነበር፤ በዚህም ዐይነት የብራናውን ጥቅል በሙሉ አቃጠለው።

24 ንጉሡም ሆነ መኳንንቱ ይህን ሁሉ ከሰሙ በኋላ ምንም ዐይነት ፍርሀት አልተሰማቸውም ወይም በሐዘን ልብሳቸውን አልቀደዱም።

25 ኤልናታን፥ ደላያና ገማርያ ንጉሡ የብራናውን ጥቅል እንዳያቃጥል ቢለምኑትም እንኳ ሊያዳምጣቸው አልፈለገም።

26 ከዚህ በኋላ ልዑሉን ይረሕምኤልን ከዐዝርኤል ልጅ ሠራያና ከዐብድኤል ልጅ ከሸሌምያ ጋር ሆኖ እኔንና ባሮክን እንዲይዝ አዘዘው፤ እኛ ግን እግዚአብሔር ሰወረን።


ኤርምያስ እንደገና የጻፈው ቃል

27-28 እኔ እየነገርኩት ባሮክ የጻፈውን የብራና ጥቅል ንጉሥ ኢዮአቄም ካቃጠለው በኋላ ሌላ የሚጠቀለል ብራና ወስጄ የቀድሞውን ቃል እንደገና እንድጽፈው እግዚአብሔር አዘዘኝ።

29 ለንጉሡም እንዲህ ብዬ እንድነግረው አዘዘኝ፦ “እነሆ አንተ የብራናውን ጥቅል አቃጥለሃል፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ መጥቶ ይህችን ምድርና በእርስዋ የሚኖሩትን ሕዝብ፥ እንዲሁም እንስሶችን ሁሉ እንደሚያጠፋ ትንቢት የተናገርከው ስለምንድን ነው?’ ብለህ ኤርምያስን ጠይቀኸዋል፤

30 ንጉሥ ኢዮአቄም ሆይ! እነሆ እግዚአብሔር ስለ አንተ የሚለው ይህ ነው፦ ‘ከዘርህ በዳዊት መንግሥት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ከቶ አይኖርም፤ ሬሳህም የትም ተጥሎ ለቀን ፀሐይ ሐሩርና ለሌሊት ቊር የተጋለጠ ይሆናል፤

31 ስለ ፈጸማችሁት ኃጢአት አንተን ራስህን፥ ልጆችህንና መኳንንትህን ሁሉ እቀጣለሁ። አንተም ሆንክ የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ሕዝብ የሰጠኋችሁን ማስጠንቀቂያ ከምንም አልቈጠራችሁትም፤ ከዚህም የተነሣ አስቀድሞ ላመጣው ያቀድኩትን መቅሠፍት ሁሉ በእናንተ ላይ አመጣባችኋለሁ።’ ”

32 ስለዚህ ሌላ የብራና ጥቅል ወስጄ ለጸሐፊዬ ለባሮክ ሰጠሁት፤ እርሱም በቃል የነገርኩትን ሁሉ ጻፈበት፤ በዚህ ዐይነት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው ብራና ተጽፎ የነበረውን ጻፈ፤ ሌሎችም ብዙ ተመሳሳይ ቃሎች ተጨምረውበታል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos