ኤርምያስ 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኤርምያስና ነቢዩ ሐናንያ 1 በዚሁ ዘመን፥ ማለትም ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር የገባዖን ሰው የሆነው የዐዙር ልጅ ሐናንያ በቤተ መቅደስ ተናገረኝ፤ በካህናቱና በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ አለኝ፦ 2 “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎአል፥ ‘የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁ፤ 3 ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚህ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን የቤተ መቅደስ ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደዚህ ስፍራ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ 4 እንዲሁም የኢዮአቄምን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ወደ ባቢሎን ተሰደው ከሄዱት ከይሁዳ ሕዝብ ጋር መልሼ አመጣዋለሁ፤ አዎ! የባቢሎንን ንጉሥ የአገዛዝ ቀንበር እሰብራለሁ፤’ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” 5 እኔም በካህናቱና በቤተ መቅደስ በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ሐናንያን እንዲህ አልኩት፦ 6 “አሜን! እግዚአብሔር እንዳልከው ያድርግ! የቤተ መቅደሱን ዕቃዎች በማምጣትና የተማረኩትን ምርኮኞች በመመለስ እግዚአብሔር አንተ የተናገርከውን ትንቢት ይፈጽም። 7 ሆኖም ለአንተና ለሕዝቡ የምናገረውን ስማ፤ 8 በጥንት ዘመን ከእኔና ከአንተ በፊት የተነሡ ነቢያት በብዙ ሕዝብና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ጦርነት፥ ራብና ቸነፈር እንደሚመጣ ትንቢት ተናግረዋል፤ 9 ነገር ግን ስለ ሰላም የተናገረ ነቢይ ቢኖር ከእግዚአብሔር የተላከ ነቢይ መሆኑ የሚታወቀው ያ የተናገረው ትንቢት እውነት ሆኖ ሲገኝ ነው።” 10 ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሐናንያ በእኔ ጫንቃ ላይ የነበረውን ቀንበር ወስዶ ሰባበረው፤ 11 በሕዝቡም ሁሉ ፊት ሲናገር፦ “በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን የአገዛዝ ቀንበር ከሕዝቡ ጫንቃ ላይ አውርዶ እንደዚህ የሚሰባብረው መሆኑን እግዚአብሔር ተናግሮአል” አለ፤ ከዚያም በኋላ እኔ ከዚያ ተነሥቼ ሄድኩ። 12 ነቢዩ ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ ጫንቃ ላይ ከሰበረ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13 “ሂድ! ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ‘እነሆ አንተ የእንጨቱን ቀንበር ለመስበር ችለሃል፤ እኔ ግን በእርሱ ፈንታ የብረት ቀንበር እተካለሁ፤ 14 በእነዚህ ሕዝቦች ሁሉ ጫንቃ ላይ የብረት ቀንበር እጭናለሁ፤ እነርሱም ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ይገዙለታል፤ ሌላው ቀርቶ የምድረ በዳ እንስሶች ሁሉ እንዲገዙለት አደርጋለሁ፤’ እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ።” 15 እኔም ይህንኑ ለሐናንያ እንዲህ ብዬ ነገርኩት፦ “ሐናንያ ሆይ! ስማ፤ አንተን እኮ እግዚአብሔር አላከህም፤ ይህንንም ሁሉ ሕዝብ ሐሰት በሆነ ነገር እንዲተማመን አድርገሃል። 16 ስለዚህም እግዚአብሔር ‘አንተን ከምድረ ገጽ አስወግድሃለሁ ይህ ሕዝብ በእኔ በአምላካቸው ላይ እንዲያምፁ በማድረግህ ምክንያት ይህ ዓመት ከመፈጸሙ በፊት ትሞታለህ’ ይላል።” 17 ነቢዩ ሐናንያም በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ። |