Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 36 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዔሳው ዘሮች
( 1ዜ.መ. 1፥34-37 )

1 ኤዶም የተባለው የዔሳው የትውልድ ታሪክ የሚከተለው ነው፤

2 ዔሳው ከነዓናውያን ሴቶችን አገባ፤ እነርሱም የሒታዊው የኤሎን ልጅ ዓዳ፥ የሒዋዊው የጺባዖን ልጅ ዐና የወለዳት ኦሆሊባማን እና፥

3 የነባዮት እኅት የነበረችው የእስማኤል ልጅ ባሴማት ናቸው።

4 ዓዳ ለዔሳው ኤሊፋዝን ወለደችለት፤ ባሴማትም ረዑኤልን ወለደችለት፤

5 ኦሆሊባማም የዑሻን፥ ያዕላምንና ቆሬን ወለደችለት። እነዚህ ሁሉ ለዔሳው በከነዓን ምድር የተወለዱለት ልጆች ናቸው።

6 ከዚህ በኋላ ዔሳው ሚስቶቹን ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፥ በቤቱ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ መንጋዎቹንና ሌሎቹንም ከብቶች ሁሉ፥ በከነዓን ሳለ ያፈራውን ንብረት ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደ።

7 ይህንንም ያደረገበት ምክንያት እርሱና ያዕቆብ ብዙ ንብረት ስለ ነበራቸው፥ የሚሰፍሩበት ምድር ለሁለት ስላልበቃ ነው፤ ሁለቱም ብዙ እንስሶች ስለ ነበሩአቸው አብረው ለመኖር አልቻሉም።

8 ስለዚህ ኤዶም የተባለው ዔሳው በተራራማው አገር በኤዶም ተቀመጠ።

9 በተራራማው አገር በኤዶም ይኖሩ የነበሩት ኤዶማውያን ቅድመ አያት የነበረው የዔሳው ዘሮች የሚከተሉት ናቸው፤

10 ዔሳው ከሚስቱ ከዓዳ ኤሊፋዝን፥ ከሚስቱ ከባሴማት ረዑኤልን ወለደ።

11 የኤልፋዝ ልጆች፦ ቴማን፥ ኦማር፥ ጸፎ፥ ጋዕታምና ቀናዝ ናቸው።

12 የዔሳው ልጅ ኤሊፋዝ ቲመናዕ የምትባል ቁባት ነበረችው፤ እርስዋ ለኤሊፋዝ ዐማሌቅን ወለደችለት፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የዓዳ የልጅ ልጆች ናቸው።

13 የረዑኤል ልጆች፦ ናሐት፥ ዘራሕ፥ ሻማና ሚዛ ናቸው፤ እነዚህም ዔሳው ባሴማት ከምትባለው ሚስቱ የወለዳቸው የልጅ ልጆች ናቸው።

14 የዐና ልጅና የጺባዖን የልጅ ልጅ የነበረችው ኦሆሊባማ ለዔሳው የወለደቻቸው ልጆች፥ የዑሽ፥ ያዕላምና ቆሬ ናቸው።

15 የዔሳው መጀመሪያ ልጅ የኤልፋዝ ነገድ አለቆች፦ ቴማን፥ ኦማር፥ ጸፎ፥ ቀናዝ፥

16 ቆሬ፥ ገዕታምና ዐማሌቅ፤ እነዚህ በኤዶም የኤልፋዝ ነገድ አለቆች ሲሆኑ፥ እነርሱም ዔሳው ከሚስቱ ከዓዳ የወለዳቸው ናቸው።

17 የዔሳው ልጅ የረዑኤል ነገድ አለቆች፦ ናሐት፥ ዘራሕ፥ ሻማና ሚዛ ሲሆኑ እነዚህ በኤዶም የረዑኤል ነገድ አለቆች ናቸው፤ እነርሱም ዔሳው ከሚስቱ ከባሴማት የወለዳቸው ናቸው።

18 ከዔሳው ሚስት ከኦሆሊባማ የተወለዱት የነገድ አለቆች፦ የዑሽ፥ ያዕላምና ቆሬ ናቸው፤ እነዚህ ከዐና ልጅ ከኦሆሊባማ የተወለዱ የዔሳው ትውልድ የነገድ አለቆች ናቸው።

19 እነዚህ ሁሉ ኤዶም የተባለው የዔሳው ልጆችና የነገድ አለቆች ናቸው።


የሤዒር ዘሮች
( 1ዜ.መ. 1፥38-42 )

20 በኤዶም ምድር ነዋሪዎች የነበሩት የሤዒር ልጆች የሖራውያን አለቆች፦ ሎጣን፥ ሾባል፥ ጺባዖን፥ ዐና፥

21 ዲሾን፥ ኤጼርና፥ ዲሻን ናቸው።

22 ሎጣን የሖሪና የሄማም ጐሣዎች ቅድመ አያት ነበረ። ሎጣን ቲምናዕ የተባለች እኅት ነበረችው።

23 የሾባል ልጆችም ዓልዋን፥ ማናሐት፥ ዔባል፥ ስፎና፥ ኦናም ናቸው።

24 የጺባዖን ልጆችም አያ እና ዐና ናቸው። ይህም ዐና የአባቱን አህዮች ሲጠብቅ በበረሓ ውስጥ የፍል ውሃ ምንጮችን ያገኘ ሰው ነው።

25 የዐናም ልጅ ዲሾን የተባለው ነው፤ ሴት ልጁም ኦሆሊባማ ትባላለች።

26 የዲሾን ልጆች ሔምዳን፥ ኤሽባን፥ ይትራንና፥ ከራን ናቸው።

27 የኤጼር ልጆች ቢልሃን፥ ዛዕዋንና፥ ዓቃን ናቸው።

28 የዲሻን ልጆች ዑፅና አራን ናቸው።

29 የሖሪው አለቆች የሚከተሉት ናቸው፤ ሎጣን፥ ሾባል፥ ጺባዖን፥ ዐና፥

30 ዲሾን፥ ኤጼር፥ ዲሻን፤ እነዚህ ሁሉ በኤዶም ምድር አለቆች የሆኑ የሖሪው ዘሮች ናቸው።


የኤዶም ነገሥታት
( 1ዜ.መ. 1፥43-54 )

31 በእስራኤል ንጉሥ መንገሥ ከመጀመሩ በፊት በኤዶም ምድር የነገሡት ነገሥታት የሚከተሉት ናቸው፤

32 የበዖር ልጅ ቤላዕ በኤዶም ነገሠ፤ የነገሠባትም ከተማ ዲንሃባ ትባል ነበር።

33 ቤላዕ በሞተ ጊዜ የቦጽራ አገር ተወላጅ የዘራሕ ልጅ ዮባብ በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ።

34 ዮባብም በሞተ ጊዜ የቴማን አገር ተወላጅ ሑሻም በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ።

35 ሑሻምም በሞተ ጊዜ የምድያምን ሰዎች በሞአብ ሜዳ ድል የመታው የበዳድ ልጅ ሀዳድ በእርሱ ተተክቶ ነገሠ፤ የነገሠባትም ከተማ ዐዊት ትባል ነበር።

36 ሀዳድ በሞተ ጊዜ የማሥሬቃ ተወላጅ ሠምላ በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ።

37 ሠምላ በሞተ ጊዜ በወንዝ አጠገብ ያለችው የረሖቦት ተወላጅ የነበረው ሻኡል በእርሱ ተተክቶ ነገሠ።

38 ሻኡል በሞተ ጊዜ የዐክቦር ልጅ በዐል ሐናን በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ።

39 የዐክቦር ልጅ ባዓል ሐናንም በሞተ ጊዜ ሀዳር በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ የነገሠባትም ከተማ ፋዑ ትባል ነበር፤ ሚስቱም የሜዛሃብ ልጅ ማጥሬድ የወለደቻት መሄጣብኤል ትባል ነበር።

40 የሚከተሉትም የዔሳው ዘር የነገድ አለቆች በየጐሣቸው ስምና በየሚኖሩበት ቦታ ስም ይጠራሉ፤ ቲምናዕ፥ ዐልዋ፥ ዬቴት፥

41 ኦሆሊባማ፥ ኤላ፥ ፊኖን፥

42 ቀናዝ፥ ቴማን፥ ሚብጻር፥

43 ማግዲኤልና ዒራም። በየመኖሪያ ስፍራቸው ስም የሚጠሩት የኤዶም አለቆች እነዚህ ናቸው። ይህም ዔሳው የኤዶማውያን አባት ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos