Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ያዕቆብ ወደ ላባ ቤት መድረሱ

1 ያዕቆብ ጒዞውን ቀጥሎ በስተምሥራቅ ወዳለው አገር ደረሰ፤

2 እዚያም በሜዳ ላይ አንድ የውሃ ጒድጓድ አየ፤ በሦስት የተከፈሉ የበግ መንጋዎች በጒድጓዱ ዙሪያ ነበሩ፤ መንጋዎቹ ውሃ የሚጠጡት ከዚሁ ጒድጓድ ነበር፤ ጒድጓዱም የሚዘጋበት ድንጋይ ትልቅ ነበር፤

3 መንጋዎቹ ሁሉ እዚያ ከተሰበሰቡ በኋላ እረኞቹ ድንጋዩን አንከባለው ከጒድጓዱ ውሃ ያጠጡአቸው ነበር፤ መንጋዎቻቸውን ካጠጡ በኋላ ግን ድንጋዩን መልሰው በጒድጓዱ አፍ ላይ ይከድኑታል።

4 ያዕቆብም እረኞቹን “ወዳጆቼ ሆይ፥ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ከካራን ነው” አሉት።

5 እርሱም “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁን?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “አዎ፥ እናውቀዋለን” አሉት።

6 እርሱም “ለመሆኑ እርሱ ደኅና ነውን?” አላቸው። እነርሱም “አዎ፥ ደኅና ነው፤ እንዲያውም ልጁ ራሔል ያቺውልህ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ነች” አሉት።

7 ያዕቆብም “ጊዜው ገና ቀን ነው፤ መንጋዎቻችሁንም ወደ ቤት የምታስገቡበት ሰዓት ገና አልደረሰም፤ ታዲያ ለምን ውሃ አጠጥታችሁ አታሰማሩአቸውም?” አለ።

8 እነርሱም “እረኞች ሁሉ መንጋዎቻቸውን ይዘው እዚህ ከመሰብሰባቸው በፊት ምንም ማድረግ አንችልም፤ ሁሉም እዚህ ከመጡ በኋላ ግን ድንጋዩን በኅብረት አንከባለን በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉት።

9 ያዕቆብም ከእረኞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ ራሔል የአባትዋን በጎች ይዛ ወደዚያ መጣች፤ እርስዋ የበጎች እረኛ ነበረች።

10 ያዕቆብ ያጐቱን የላባን በጎች እየነዳች ስትመጣ ራሔልን አይቶ ወደ ጒድጓዱ ሄደ፤ ጒድጓዱ የተከደነበትንም ድንጋይ አንከባሎ በጎቹን አጠጣቸው።

11 ከዚህ በኋላ ራሔልን ሳማት፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ አለቀሰ፤

12 “እኔ የአባትሽ እኅት የርብቃ ልጅ ነኝ” አላት። እርስዋም ለአባቷ ልትነግር ሮጣ ሄደች።

13 ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን በሰማ ጊዜ ሊቀበለው ፈጥኖ ሄደ፤ ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ ወደ ቤት አመጣው፤ ያዕቆብ የሆነውን ሁሉ ለላባ ነገረው፤

14 ላባም “በእርግጥ አንተ ቅርብ የሥጋ ዘመዴ ነህ” አለው፤ ያዕቆብም አንድ ወር ያኽል ከአጐቱ ጋር ተቀመጠ።


ያዕቆብ ስለ ራሔልና ስለ ልያ ላባን ማገልገሉ

15 ላባ ያዕቆብን “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለኝ አይገባህም፤ ስለዚህ ምን ያኽል ደመወዝ ላስብልህ?” አለው።

16 ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ታላቂቱ ልያ፤ ታናሽቱ ራሔል ይባሉ ነበር።

17 ልያ ዐይነ ልም ስትሆን፥ ራሔል ግን ቁመናዋ የሚያምር የደስ ደስ ያላት ነበረች።

18 ያዕቆብ ራሔልን እጅግ ስለ ወደዳት “ራሔልን ብትድርልኝ ሰባት ዓመት አገለግልሃለሁ” አለ።

19 ላባም “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጥህ ይሻለኛል፤ እሺ ተስማምቼአለሁ፤ እዚሁ ከእኔ ጋር ኑር” አለው።

20 ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት ሰባት ዓመት አገለገለ፤ ይሁን እንጂ ራሔልን በጣም ይወዳት ስለ ነበር የቈየበት ጊዜ ጥቂት ቀን ብቻ መስሎ ታየው።

21 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ላባን “እነሆ፥ የአገልግሎት ዘመኔ ተፈጽሞአል፤ ሚስት እንድትሆነኝ ልጅህን ስጠኝ” አለው።

22 ላባም የሠርግ ድግስ አዘጋጅቶ በአቅራቢያው የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ ጠራ።

23 ነገር ግን በመሸ ጊዜ ላባ በራሔል ምትክ ልያን ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም ወደ ልያ ገባ።

24 ላባ ሴት አገልጋዩን ዚልፋን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለልያ ሰጣት።

25 በማግስቱ ጠዋት ያዕቆብ አብራው ያደረችው ልያ መሆንዋን ባወቀ ጊዜ ወደ ላባ ሄዶ “ይህ ያደረግህብኝ ነገር ምንድን ነው? ያገለገልኩህ ራሔልን ለማግኘት አልነበረምን? ታዲያ ለምን አታለልከኝ?” አለው።

26 ላባም “ታላቂቱ ሳትዳር፥ ታናሺቱን መዳር የአገራችን ልማድ አይደለም፤

27 የልያ ሠርግ ሰባት ቀን እስኪሞላው ድረስ ጠብቅ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰባት ዓመት የምታገለግለኝ ከሆነ ራሔልን እሰጥሃለሁ” አለው።

28 ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋር ሰባት ቀን ተሞሽሮ ከቈየ በኋላ፥ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት።

29 ላባ ሴት አገልጋዩን ባላን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለራሔል ሰጣት።

30 ያዕቆብ ወደ ራሔልም ገባ፤ ከልያም አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያ በኋላ ላባን ሰባት ዓመት አገለገለው።


ለያዕቆብ የተወለዱ ልጆች

31 ልያ የራሔልን ያኽል እንዳልተወደደች እግዚአብሔር ባየ ጊዜ ልጅ መውለድ እንድትችል ማሕፀንዋን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መኻን ሆነች፤

32 ልያ ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ “እግዚአብሔር መከራዬን ተመለከተ፤ ከእንግዲህስ ወዲያ ባሌ ይወደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል አለችው።

33 እንደገና ፀነሰችና ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ “እግዚአብሔር እንዳልተወደድኩ ሰማ፤ ይህንንም ልጅ ደግሞ ሰጠኝ” ስትል ስሙን ስምዖን አለችው።

34 እንደገና ፀነሰችና ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ “እንግዲህ ሦስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድኩለት አሁን ባሌ ከእኔ ጋር በፍቅር ይጠመዳል” ስትል ስሙን ሌዊ አለችው፤

35 እንደገና ፀነሰችና ወንድ ልጅ ወለደች፤ “አሁንስ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ስትል ስሙን ይሁዳ አለችው፤ ከዚህ በኋላ መውለድ አቋረጠች።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos