Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 44 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የተዘጋው በር

1 ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር።

2 ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል፤ አይከፈትምም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።

3 መስፍኑ ብቻ በጌታ ፊት ምግብ ለመብላት ይቀመጥበታል፤ በበሩ መተላለፊያ መንገድ ይገባል በዚያም መንገድ ይወጣል።


ወደ መቅደሱ ስለመግባት

4 በሰሜኑ በር መንገድ ወደ ቤቱ ፊት ለፊት አገባኝ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆ የጌታ ክብር የጌታን ቤት ሞልቶት ነበር፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ።

5 ጌታም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጌታ ቤት ሥርዓት ሁሉ እና ሕጉን ሁሉ የምናገርህን ሁሉ ልብ አድርግ በዓይንህ ተመልከት በጆሮህም ስማ፤ የቤቱን መግቢያ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ።

6 ለዓመፀኛው ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ርኩሰታችሁ ከእንግዲህ ሁሉ ያብቃ፥

7 ምግቤን፥ ስብንና ደምን፥ በምታቀርቡበት ጊዜ ቤቴን እንዲያረክሱ በመቅደሴ ውስጥ እንዲሆኑ ያልተገረዘ ልብ፥ ያልተገረዘ ሥጋ ያላቸውን ባዕዳንን አግብታችኋል፥ በርኩሰታችሁም ሁሉ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል።

8 በመቅደሴ ውስጥ ሥርዓቴን ጠባቂዎች ለራሳችሁ አስቀመጣችሁ እንጂ የተቀደሰውን ነገሬን ሥርዓት አልጠበቃችሁም።

9 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ልጆች መካከል ያለ የባዕድ ልጅ ሁሉ፥ ልቡ ያልተገረዘ ሥጋው ያልተገረዘ የባዕድ ልጅ ሁሉ ወደ መቅደሴ አይግባ።

10 እስራኤል እኔን ከመከተል ርቀው በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ ጣዖታቸውን ተከትለው ከእኔ የራቁት ሌዋውያን ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ።

11 በመቅደሴ ውስጥ አገልጋዮች፥ በቤቱም በሮች ዘበኞች ይሆናሉ፥ በቤቱም ውስጥ ያገለግላሉ፤ ለሕዝቡም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና መሥዋዕትን ያርዳሉ፥ ሊያገለግሉአቸውም በፊታቸው ይቆማሉ።

12 በጣዖቶቻቸው ፊት አገልግለዋቸው ነበሩና፥ ለእስራኤልም ቤት የኃጢአት ዕንቅፋት ሆነዋልና ስለዚህ እጄን በላያቸው አንሥቻለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይሸከማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

13 በክህነት ሊያገለግሉኝ ወደ እኔ አይቀርቡም፥ ወደተቀደሰው ነገሬና ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አይቀርቡም፤ ስድባቸውንና የሠሩትን ርኩሰታቸውን ይሸከማሉ።

14 ሆኖም ለአገልግሎቱ ሁሉና በእርሱ ውስጥ ለሚደረገው ሁሉ የቤቱን ሥርዓት ጠባቂዎች አደርጋቸዋለሁ።


ስለ ሌዋውያን ካህናት

15 የእስራኤል ልጆች ከእኔ በራቁ ጊዜ የመቅደሴን ሥርዓት የጠበቁ የሳዶቅ ልጆች ሌዋውያን ካህናት ሊያገለግሉኝ ወደ እኔ ይቀርባሉ፤ ስቡንና ደሙን ወደ እኔ ሊያቀርቡ በፊቴ ይቆማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

16 ወደ መቅደሴም ይገባሉ እኔን ለማገልገል ወደ ገበታዬ ይቀርባሉ ሥርዓቴን ይጠብቃሉ።

17 ወደ ውስጠኛው አደባባይ በር በገቡ ጊዜ የተልባ እግር ልብስ ይልበሱ፤ በውስጠኛው አደባባይ በርና በቤቱ ውስጥ ባገለገሉ ጊዜ አንዳች የበግ ጠጉር በላያቸው አይሁን።

18 በራሳቸው ላይ የተልባ እግር መጠምጠሚያ ይሁን፥ በወገባቸውም ላይ የተልባ እግር ሱሪ ይሁን፤ የሚያልብ ነገር አይታጠቁ።

19 ወደ ውጭው አደባባይ ወደ ሕዝቡ በሚወጡበት ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን ያውልቁ፥ በተቀደሰው ቤት ውስጥ ያኑሩት፥ ሕዝቡንም በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ሌላ ልብስ ይልበሱ።

20 ራሳቸውን አይላጩ፥ የተያዘ ጠጉራቸውንም አይልቀቁትም፥ ነገር ግን የራሳቸውን ጠጉር ይከርከሙ።

21 ካህናቱ ሁሉ ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ አይጠጡ።

22 መበለቲቱንና የተፈታችውን ለሚስትነት አይውሰዱ፤ነገር ግን ከእስራኤል ቤት ዘር የሆነችውን ድንግል ወይም የካህን ሚስት የነበረችውን መበለት ይውሰዱ።

23 ሕዝቤን ቅዱስ በሆነውና በረከሰው መካከል እንዲለዩ ያስተምሩ፥ ንጹሕ በሆነውና ንጹሕ ባልሆነው መካከል እንዲለዩ ያሳዩአቸው።

24 ክርክር በሚነሣበት ጊዜ ለመፍረድ ይቁሙ፤ በፍርዴ ይፍረዱ፤ በበዓላቴ ሁሉ ሕጌንና ሥርዓቴን ይጠብቁ፥ ሰንበታቴንም ይቀድሱ።

25 እንዳይረክሱ ወደ ሞተ ሰው አይግቡ፤ ነገር ግን ለአባት ወይም ለእናት ወይም ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ ወይም ለወንድም ወይም ላላገባች እኅት ይርከሱ።

26 ከነጻ በኋላ ሰባት ቀን ይቁጠሩለት።

27 በመቅደስም ውስጥ ሊያገለግል ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቅርብ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

28 ርስት ይሆንላቸዋል፤ ርስታቸው እኔ ነኝ፤ በእስራኤልም ግዛት አትስጡአቸው፤ ግዛታቸው እኔ ነኝ።

29 የእህሉን ቁርባን፥ የኃጢአትን መሥዋዕትና የበደልን መሥዋዕት ይበላሉ፤ በእስራኤልም እርም የሆነው ነገር ሁሉ ለእነርሱ ይሆናል።

30 የበኩራቱ ሁሉ መጀመሪያ፥ ስጦታ ሁሉ፥ ስጦታዎቻችሁ ሁሉ፥ ለካህናት ይሆናል፤ በቤትህም ውስጥ በረከት እንዲያድር የሊጣችሁን በኵራት ለካህን ትሰጣላችሁ።

31 ካህናቱ የሞተ ወይም ሌላ አውሬ የገደለውን ወፍ ወይም እንስሳ አይብሉ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos