Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የይሁዳ መማረክ በስዕል ተገለፀ

1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

2 የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፥ እንዲያዩ ዐይን አላቸው ነገር ግን አያዩም፥ እንዲሰሙም ጆሮ አላቸው ነገር ግን አይሰሙም፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።

3 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ ጓዝ ለራስህ አዘጋጅ፥ እያዩህም በቀን ወደ ምርኮ ሂድ፥ በፊታቸውም እንደ ምርኮኛ ከስፍራህ ወደ ሌላ ስፍራ ሂድ፥ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑም ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል።

4 ጓዝህን እንደ ስደተኛ ጓዝ እያዩህ በቀን አውጣው፥ በማታም እያዩህ ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ።

5 እያዩህም ግንቡን ቦርቡረው፥ በእርሱም አውጣው።

6 ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና እያዩህ በትከሻህ ላይ ተሸከመው፥ በጨለማም ይዘኸው ውጣ፥ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።

7 እኔም እንደታዘዝኩት አደረግሁ፥ በቀንም ጓዙን እንደ ስደተኛ ጓዝ አወጣሁ፥ በምሽትም ጊዜ ግንቡን በእጄ ቦረቦርሁት፥ እያዩኝም በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ በጨለማ አወጣሁት።

8 በማግስቱም የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

9 የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት፥ ዓመፀኛ ቤት፦ ምን እያደረግህ ነው? አላሉህምን?

10 እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ለሚኖረው መስፍንና በውስጧ ለሚኖሩ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ነው።

11 እንዲህም በላቸው፦ እኔ ምልክታችሁ ነኝ፥ እኔ እንዳደረግሁት እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱም ወደ ስደት ወደ ምርኮ ይሄዳሉ።

12 በመካከላቸውም ያለው ልዑል በትከሻው ላይ ተሸክሞ በጨለማ ይወጣል፥ በዚያም ሊወጡ ግንቡን ይቦረቡራሉ፥ በዓይኑም ምድሪቱን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል።

13 መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፥ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፥ ሆኖም አያያትም በዚያም ይሞታል።

14 በዙሪያው ያሉ ረዳቶቹና ወታደሮቹን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፥ ከኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።

15 በአሕዛብ መካከል ስበትናቸው፥ በአገሮችም ስዘራቸው፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

16 በሚሄዱባቸው አሕዛብ መካከል ርኩሰታቸውን ሁሉ እንዲናገሩ ከእነርሱ ጥቂቶች ከሰይፍ፥ ከራብና ከቸነፈር አስቀራለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።


ፍርድ ተፈፀመ እንጂ አልተላለፈም

17 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

18 የሰው ልጅ ሆይ፥ ምግብህን በድንጋጤ ብላ፥ ውኃህንም በመንቀጥቀጥና በስጋት ጠጣ፤

19 ለምድሪቱም ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር በእስራኤልም ምድር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩት እንዲህ ይላል፦ በሚኖሩባት ሰዎች ሁሉ ግፍ ምድሪቱ ከነሞላዋ ስለምትጠፋ ምግባቸውን በስጋት ይበላሉ ወኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ።

20 ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ይጠፋሉ፥ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

21 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

22 የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር፦ “ቀኖቹ ረዝመዋል፥ ራእይም ሁሉ ጠፍቶአል” የምትሉት ይህ ምሳሌ ምንድነው?

23 ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፥ አንተ ግን፦ ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቧል በላቸው።

24 ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም።

25 ነገር ግን እኔ ጌታ የምናገረውን ቃል እናገራለሁ፥ ይፈጸማልም፥ ደግሞም አይዘገይም፥ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመዋለሁም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

26 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

27 የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ የእስራኤል ቤት እንዲህ ይላሉ፦ የሚያየው ራእይ ለብዙ ዘመን ነው፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል።

28 ስለዚህም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos