ቃል ኪዳኑ በሴኬም ታደሰ1 ከዚያም ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ በሴኬም ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ፈራጆችና ሹማምት ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። 2 ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ፣ የአብርሃምንና የናኮርን አባት ታራን ጨምሮ ከብዙ ዘመን በፊት ከወንዙ ማዶ ኖሩ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። 3 እኔ ግን አባታችሁን አብርሃምን ከወንዙ ማዶ ካለው ምድር አምጥቼ፣ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሮቹን አበዛሁለት፤ ይሥሐቅንም ሰጠሁት። 4 ለይሥሐቅ ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም ኰረብታማውን የሴይርን ምድር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብና ልጆቹ ግን ወደ ግብጽ ወረዱ። 5 “ ‘ከዚያም ሙሴንና አሮንን ላክሁ፤ ባመጣሁት መቅሠፍት ግብጻውያንን አስጨንቄ፣ እናንተን ከዚያ አወጣኋችሁ። 6 አባቶቻችሁን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ወደ ባሕሩ መጣችሁ፤ ግብጻውያንም በሠረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ተከታተሏቸው። 7 እነርሱ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም በእናንተና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረገ። ባሕሩን በላያቸው አመጣ፤ አሰጠማቸውም። በግብጻውያን ላይ ያደረግሁትንም ራሳችሁ በዐይናችሁ አያችሁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ኖራችሁ። 8 “ ‘በምሥራቅ ዮርዳኖስ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው፤ ከፊታችሁ አጠፋኋቸው፤ እናንተም ምድራቸውን ወረሳችሁ። 9 የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤልን ለመውጋት ተነሣ፣ እናንተንም መጥቶ ይረግማችሁ ዘንድ ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም መልእክተኛ ላከ፤ 10 እኔ ግን በለዓምን ልሰማው አልፈለግሁም፤ ስለዚህ ደግሞ ደጋግሞ መረቃችሁ፤ እኔም፤ ከባላቅ እጅ ታደግኋችሁ። 11 “ ‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን እንደ ወጓችሁ ሁሉ፣ የኢያሪኮም ገዦች ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው። 12 በፊታችሁ ተርብ ላክሁ፤ ይህም እነርሱንና ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ጭምር ከፊታችሁ አሳደደ፤ ይህ ደግሞ በራሳችሁ ሰይፍና ቀስት ያደረጋችሁት አይደለም። 13 ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ። እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’ 14 “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብጽ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ። 15 እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” 16 ከዚያም ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሌሎችን አማልእክት ለማምለክ ብለን እግዚአብሔርን መተው ከእኛ ይራቅ። 17 እኛንና የቀደሙ አባቶቻችንን ከዚያ ከጦርነት ምድር ከግብጽ ያወጣን፣ በፊታችንም እነዚያን ታላላቅ ምልክቶች ያደረገ ማነው? ራሱ አምላካችን እግዚአብሔር አይደለምን? በጕዟችን ላይና ባለፍንባቸውም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የጠበቀን እርሱ ነው። 18 እንዲሁም እግዚአብሔር በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ጨምሮ ሕዝቦችን ሁሉ ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ አምላካችን ነውና።” 19 ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ እርሱ ቅዱስ አምላክና፤ ቀናተኛም አምላክ ነው፤ ዐመፃችሁን ወይም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልም። 20 እግዚአብሔርን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን የምታመልኩ ከሆነ፣ መልካም ነገር ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችኋልም።” 21 ሕዝቡ ግን ኢያሱን፣ “የለም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት። 22 ከዚያም ኢያሱ፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን ለማምለክ መርጣችኋልና በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን ምስክሮች ነን” ሲሉ መለሱ። 23 ኢያሱም፣ “እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር መልሱ” አላቸው። 24 ሕዝቡም ኢያሱን፣ “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እንታዘዝለታለንም” አሉት። 25 በዚያ ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋራ ቃል ኪዳን አደረገ፤ የሚመሩበትንም ደንብና ሥርዐት እዚያው ሴኬም ሰጣቸው። 26 ኢያሱም እነዚህን ቃሎች እግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ጻፋቸው፤ ትልቅ ድንጋይም ወስዶ በባሉጥ ዛፍ ሥር፣ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ስፍራ አጠገብ አቆመው። 27 ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ፣ “እነሆ፤ ይህ ድንጋይ፣ እግዚአብሔር የተናገረንን ሁሉ ሰምቷል፣ በእኛም ይመሰክርብናል፤ እናንተም በአምላካችሁ ዘንድ እውነተኞች ሆናችሁ ባትገኙ ምስክር ይሆንባችኋል” አላቸው። 28 ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ ወደየርስቱ እንዲሄድ አሰናበተ። ኢያሱ በተሰፋዪቱ ምድር ተቀበረ24፥29-31 ተጓ ምብ – መሳ 2፥6-9 29 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። 30 በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው፣ ከገዓስ ተራራ በስተሰሜን ባለችው በራሱ ርስት በተምናሴራ ቀበሩት። 31 ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ከኢያሱም በኋላ በሕይወት በኖሩትና እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ በሚያውቁት ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አመለኩ። 32 እስራኤላውያን ከግብጽ ያወጡት የዮሴፍ ዐፅም፣ ያዕቆብ ከሰኬም አባት ከኤሞር በመቶ ሰቅል ብር በገዛው በሴኬም ምድር ተቀበረ፤ ይህችም የዮሴፍ ዘሮች ርስት ሆነች። 33 እንዲሁም የአሮን ልጅ አልዓዛር ሞተ፤ እርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በሚገኘው ለልጁ ለፊንሐስ በዕጣ በደረሰው በጊብዓ ምድር ተቀበረ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.