ስለ ሐሰት ራእይ ፍጻሜ ትንቢት1 በዚያ ቀን ለዳዊት ቤትና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ከኃጢአትና ከርኩሰት የሚያነጻ ምንጭ ይፈልቃል። 2 በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፤ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ። 3 አሁንም ቢሆን ማንም ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባቱና እናቱ፦ “አንተ በጌታ ስም ሐሰትን ተናግረሃልና በሕይወት አትኖርም” ይሉታል። ትንቢትንም ሲናገር የወለዱት አባትና እናቱ ይወጉታል። 4 በዚያም ቀን እያንዳንዱ ነቢይ ስለሚናገረው ትንቢት ስለ ራእዩ ያፍራል፥ ለማታለልም የማቅ ልብስ አይለብሱም። 5 ነገር ግን እያንዳንዱ፦ “ከታናሽነቴ ጀምሮ አገልጋይ ነበርኩ፥ መሬት አራሽ ነኝ እንጂ ነቢይ አይደለሁም” ይላል። 6 ማንም ሰው፦ “ይህ በእጅህ መካከል ያለ ቁስል ምንድነው?” ብሎ ቢጠይቀው፥ እያንዳንዱም፦ “በወዳጆቼ ቤት የቈሰልኩት ቁስል ነው” ይላል። ስለ ሰይፍ መዝሙር7 ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ በጎቹም እንዲበተኑ እረኛውን ምታ፤ እጄንም በታናናሾች ላይ አዞራለሁ። 8 በምድርም ሁሉ ላይ ሁለት ሦስተኛው ተቈርጠው ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ፤ አንድ ሦስተኛው ክፍልም በእርሷ ይቀራል። 9 አንድ ሦስተኛውን ክፍል ወደ እሳት አስገባለሁ፤ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፤ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ፤ እኔም፦ “ይህ ሕዝቤ ነው” እላለሁ፥ እርሱም፦ “ጌታ አምላኬ ነው” ይላል። |