La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


ሆሴዕ 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
ሆሴዕ 14

ነቢዩ ሆሴዕ ንስሐ እንዲገቡ መለመኑ

1 ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና በደልዋን ትሸከማለች፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ሕፃኖቻቸውም ይፈጠፈጣሉ፥ እርጉዞቻቸውም ይቀደዳሉ።

2 እስራኤል ሆይ! በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ ጌታ ተመለስ።

3 ከእናንተ ጋር ቃላትን ውሰዱ፥ ወደ ጌታም ተመለሱ፥ እንዲህም በሉት፦ “በደልን ሁሉ አስወግድ፥ በቸርነትም ተቀበለን፥ በእንቦሳም ፋንታ የከንፈራችንን ፍሬ እንሰጣለን።

4 አሦር አያድነንም፤ በፈረስ ላይ አንቀመጥም፤ ድሀ አደጉም በአንተ ዘንድ ምሕረትን ያገኛልና ከእንግዲህ ወዲህ ለእጆቻችን ሥራ፦ ‘አምላኮቻችን’ ናችሁ አንላቸውም።”

5 ቁጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ከዳተኝነታቸውን እፈውሳለሁ፥ በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ።

6 ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፤ እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሮቹን ይሰድዳል።

7 ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፥ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል።

8 ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፤ እንደ አትክልት ስፍራ ይለመልማሉ፤ እንደ ወይንም ተክል ያብባሉ፤ መዓዛቸውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል።

9 ኤፍሬም ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ከጣዖታት ጋር እኔ ምን አደርጋለሁ? እኔ እመልስለታለሁ፥ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፤ ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል።

10 እነዚህን ነገሮች የሚያስተውል ጠቢብ ማን ነው? የሚያውቃቸውስ አስተዋይ ማን ነው? የጌታ መንገድ ቅን ነው፥ ጻድቃንም ይሄዱበታል፤ ዓመፀኞች ግን ይወድቁበታል።

Mostrar Biblia Interlineal