1 በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም፥ በአካዝና በሕዝቅያስም ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው። የነቢዩ ሆሴዕ ቤተሰብ2 ጌታ መጀመሪያ በሆሴዕ በተናገረ ጊዜ፥ ጌታ ሆሴዕን፦ “ምድሪቱ ከጌታ ርቃ ታላቅ ዝሙት አድርጋለችና ሂድ፤ አመንዝራን ሴት ውሰድና አግባ፤ የዝሙትም ልጆች ይኑሩህ፥” አለው። 3 እርሱም ሄዶ የዴቤላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርሷም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደችለት። 4 ጌታም እንዲህ አለው፦ “ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በኢዩ ቤት ላይ እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፤ 5 በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ።” 6 ዳግመኛም ፀነሰች ሴት ልጅም ወለደች። ጌታም እንዲህ አለው፦ “የእስራኤልን ቤት ፈጽሞ ይቅር እንድላቸው ከእንግዲህ ወዲህ ርኅራኄ የለኝምና ስምዋን ሎሩሃማ ብለህ ጥራት፤ 7 ነገር ግን የይሁዳን ቤት እምራለሁ፤ እነርሱንም በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በጦርነት ወይም በፈረሶች ወይም በፈረሰኞች ሳይሆን በአምላካቸው በጌታ አድናቸዋለሁ።” 8 ሎሩሃማንም ጡት ባስጣለች ጊዜ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። 9 ጌታም፦ “ሕዝቤ አይደላችሁምና፥ እኔም አምላካችሁ አይደለሁምና ስሙን ሎዓሚ ብለህ ጥራው፥” አለው። |