La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


2 ጢሞቴዎስ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
2 ጢሞቴዎስ 3

በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚሆነው የሰዎች ክፉ ጠባይ

1 ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚያስጨንቁ ጊዜያት እንደሚመጡ ይህን እወቅ።

2 ሰዎች እንዲህ ይሆናሉና፤ ራሳቸውን የሚወዱ፥ ገንዘብን ወዳጆች፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥

3 ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይቈጣጠሩ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥

4 ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተወጠሩ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ፥

5 የሃይማኖትን መልክ የያዙ ነገር ግን ኃይሉን የካዱ ሆነው ይገኛሉ፤ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ራቅ።

6 ከእነርሱም መካከል በየቤቱ እየተሽሎኮሎኩ በመግባት የኃጢአታቸው ሸክም የከበደባቸውንና በልዩ ልዩ ምኞትም ውስጥ የሚዋዠቁትን ደካማ ሴቶችን የሚያጠምዱ ይገኙባቸዋል።

7 እንዲህ ያሉት ሴቶች ግን ሁልጊዜ እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ከቶ ሊደርሱ የማይችሉ ናቸው።

8 ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው በእምነትም ረገድ ተፈትነው የወደቁ ሰዎች ሆነው እውነትን ይቃወማሉ።

9 ዳሩ ግን እነዚያ ሁለቱ ተቃዋሚዎች እንደሆኑት እንዲሁ የእነዚህም ሰዎች ሞኝነት ለሁሉም ሰው ስለሚገለጥ አይሳካላቸውም።

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው የመጨረሻ ምክር

10 አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን ዓላማዬንም፥ እምነቴንም፥ ትዕግሥቴንም፥ ፍቅሬንም፥ መጽናቴንም፥

11 ስደቴንም፥ መከራዬንም ተከተልህ፤ በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የደረሰብኝን ነገርና የታገሥሁትን ስደት ታውቃለህ፤ ጌታ ግን ከሁሉም አዳነኝ።

12 በእርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ለመኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።

13 ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አስመሳዮች እያታለሉና እየተታለሉ ከክፋት ወደ ባሰ ክፋት ይሄዳሉ።

14 አንተ ግን በተማርህበትና በጽኑ ባመንኸበት ነገር ሳትናወጥ ኑር፤ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤

15 እንዲሁም ከሕፃንነትህ አንሥቶ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ወደሚገኘው መዳን የሚመራህን ጥበብ ሊሰጡህ የሚያስችሉትን ቅዱስ መጻሕፍትን አውቀሃልና።

16 ቅዱስ መጸሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ አነሣሽነት የተገለጠ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማርና ለመገሠጽ፥ ስሕተትንም ለማረም፥ ሰውንም በጽድቅ መንገድ ለማለማመድ ያገለግላል፤

17 በዚህም የእግዚአብሔር ሰው በችሎታው ፍጹም እንዲሆንና ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ይጠቅማል።

Mostrar Biblia Interlineal