La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


2 ነገሥት 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
2 ነገሥት 1

ነቢዩ ኤልያስና ንጉሥ አካዝያስ

1 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ።

2 በዚህም ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ በሰማርያ ቤተ መንግሥቱ ሳለ ከሰገነቱ ላይ ወድቆ በብርቱ ስለ ቆሰለ ታሞ ነበር፤ እርሱም “እኔ ከዚህ ሕመም እድን ወይም አልድን እንደሆነ በፍልስጥኤም የዔክሮን ከተማ አምላክ የሆነውን ብዔልዜቡልን ጠይቃችሁልኝ ኑ” ብሎ መልእክተኞቹን ላከ።

3 ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ተነሥተህ የሰማርያ ንጉሥ አካዝያስ የላካቸውን መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣ፤ እንዲህም ብለህ ንገራቸው፤ ‘የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱት፥ በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብላችሁ በማሰብ ነውን?’

4 ስለዚህም እግዚአብሔር፥ ‘እነሆ አንተ ትሞታለህ እንጂ አትፈወስም! ከተኛህበት አልጋም አትነሣም! ብሎሃል’ በሉት።” ስለዚህ ኤልያስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤

5 መልእክተኞቹም ወደ ንጉሡ ተመልሰው ሄዱ፤ ንጉሡም “ስለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

6 እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አንድ ሰው በመንገድ አግኝቶን ወደ አንተ ተመልሰን እንድንመጣና እግዚአብሔር ስለ አንተ የተናገረውን እንድናስረዳህ አዘዘን፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፤ ‘የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክህበት ምክንያት ምንድነው? በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብለህ በማሰብህ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከዚህ ሕመም አትፈወስም! ከተኛህበትም አልጋ አትነሣም!’”

7 ንጉሡም “በመንገድ ያገኛችሁትና ይህን ቃል የነገራችሁ ያ ሰው እንዴት ያለ ነው?” ሲል ጠየቃቸው።

8 እነርሱም “ጠጉራም ልብስ ለብሶ በወገቡ ዙሪያ የጠፍር ቀበቶ የታጠቀ ነው” ሲሉ መለሱለት። ንጉሡም “እርሱማ ኤልያስ ነው!” አለ።

9 ከዚህም በኋላ ንጉሡ አንዱን የጦር መኰንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሄዶ ኤልያስን ይዞ ያመጣለት ዘንድ አዘዘው፤ መኰንኑም ኤልያስን በአንድ ኰረብታ ላይ ተቀምጦ አገኘውና “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው።

10 ኤልያስም “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ!” አለው፤ በዚያም ጊዜ ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ወርዶ መኰንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ።

11 ንጉሡም እንደገና ሌላውን መኰንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ላከ፤ እርሱም ወደ ኤልያስ ወጥቶ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! አሁኑኑ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል!” አለው።

12 ኤልያስም “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ!” አለው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር እሳት መኰንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ።

13 ንጉሡም ለሦስተኛ ጊዜ ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሌላ መኰንን ላከ፤ ይህኛው መኰንን ግን ወደ ኰረብታው በመውጣት በኤልያስ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት ሰዎች ምሕረት አድርግልን! ሕይወታችንንም ከሞት አድን!

14 ሌሎቹን ሁለት መኰንኖችና ተከታዮቻቸውን ሁሉ ከሰማይ የወረደ እሳት በልቶአቸዋል፤ ለእኔ ግን እባክህ ምሕረት አድርግልኝ!”

15 በዚህም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ኤልያስን “ከእርሱ ጋር አብረህ ውረድ፤ ከቶም አትፍራ” አለው። ስለዚህም ኤልያስ ከመኰንኑ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ፤

16 “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘በእስራኤል አምላክ እንደሌለ በመቁጠር፥ የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን እንዲጠይቁልህ መልእክተኞች በመላክህ ምክንያት ትሞታለህ እንጂ አትድንም!’” አለው።

17 እግዚአብሔር በኤልያስ አማካይነት በተናገረውም ቃል መሠረት አካዝያስ ሞተ፤ አካዝያስ ወንዶች ልጆች ስላልነበሩት በእርሱ እግር ተተክቶ ወንድሙ ኢዮራም ነገሠ፤ ይህም የሆነው የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ነበር።

18 ንጉሥ አካዝያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።

Mostrar Biblia Interlineal