ሚክያስ 7:3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም እጆቹ ክፉ ለማድረግ ሠልጥነዋል፤ ገዥው እጅ መንሻ ይፈልጋል፤ ፈራጁ ጕቦ ይቀበላል፤ ኀይለኞች ያሻቸውን ያስፈጽማሉ፤ ሁሉም አንድ ላይ ያሤራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እጆቻቸው ክፉ ለማድረግ የተለማመዱ ናቸው፤ ልዑሉና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፤ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጉናሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እጆቻቸው ክፉ ነገርን ለማድረግ የተለማመዱ ናቸው፤ ባለ ሥልጣኑና ዳኛው ጉቦ ይጠይቃሉ፤ ኀይለኛ ፍላጎቱን በግዴታ ተግባራዊ ያስደርጋል፤ በዚህም ዐይነት ሁሉም ፍርድን ያጣምማሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እጆቻቸውን ለክፋት ያነሣሉ፥ አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፥ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጕናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እጆቻቸውን ለክፋት ያነሣሉ፥ አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፥ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጕናሉ። |
ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጕቦን ይወድዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም።
በምድር ላይ የሚኖረውን ሕዝብ ስለ ኀጢአቱ ለመቅጣት፣ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያው ወጥቶ ይመጣል፤ ምድር በላይዋ የፈሰሰውን ደም ትገልጣለች፤ የተገደሉትንም ከእንግዲህ አትሸሽግም።
“ሕዝቤ ቂሎች ናቸው፤ እኔን አያውቁኝም። ማስተዋል የጐደላቸው፣ መረዳትም የማይችሉ ልጆች ናቸው። ክፋትን ለማድረግ ጥበበኞች፣ መልካም መሥራት ግን የማያውቁ።”
ስለዚህ ሚስቶቻቸውንም ለሌሎች ወንዶች እሰጣለሁ፤ ዕርሻዎቻቸውንም ለባዕዳን እሰጣለሁ፤ ከታናሹ እስከ ታላቁ ድረስ፣ ሁሉም ተገቢ ላልሆነ ጥቅም ይስገበገባሉ፤ ነቢያትና ካህናትም እንዲሁ፤ ሁሉም ያጭበረብራሉ።
በመካከልሽ ያሉ ሰዎች ደም ለማፍሰስ ጕቦ ይቀበላሉ፤ አንቺም ዐራጣና ከፍተኛ ወለድ በመውሰድ ከባልንጀራሽ የማይገባ ትርፍ ዘረፍሽ፤ እኔንም ረስተሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
እርሱም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፤ “የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኀጢአት እጅግ በዝቷል፤ ምድሪቱ በደም ተጥለቅልቃለች፤ ከተማዪቱም ግፍን ተሞልታለች። እነርሱ፣ ‘እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቷታል፤ እግዚአብሔር አያይም’ ይላሉ፤
ኀጢአታችሁ ምንኛ ታላቅ እንደ ሆነ፣ በደላችሁም የቱን ያህል እንደ በዛ እኔ ዐውቃለሁና። ጻድቁን ትጨቍናላችሁ፤ ጕቦም ትቀበላላችሁ፤ በፍርድ አደባባይም ከድኻው ፍትሕ ትነጥቃላችሁ።
መሪዎቿ በጕቦ ይፈርዳሉ፤ ካህናቷ ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ፤ ነቢያቷም ለገንዘብ ይጠነቍላሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈውም፣ “እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም” ይላሉ።
ስለዚህ ጊዜው ሳይደርስ በምንም ነገር አትፍረዱ፤ ጌታ እስኪመጣ ጠብቁ። እርሱ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያመጣዋል፤ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውንም ሐሳብ ይገልጠዋል። በዚያ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ምስጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።