ዮሐንስ 1:14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ዐደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በእኛም ዘንድ አደረ፤ ጸጋንና እውነትን የተመላውን፥ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብሩንም አየን። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በመካከላችን ኖረ፤ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ እንዳለው ያለውን ክብሩን አይተናል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛም አደረ፤ ለአባቱ አንድ እንደ ሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን፤ ጸጋንና እውነትን የተመላ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። |
በፊቱ እንደ ቡቃያ፣ ከደረቅም መሬት እንደ ወጣ ሥር በቀለ፤ የሚስብ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤ እንድንወድደውም የሚያደርግ መልክ አልነበረውም።
ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋራ ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ?
ጲላጦስም፣ “ታዲያ፣ ንጉሥ ነህ ማለት ነዋ!” አለው። ኢየሱስም፣ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል” አለው።
በርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወድዷልና።
ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ ይህም እንጀራ፣ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”
ኢየሱስንም ከሙታን በማስነሣቱ ለእነርሱ የገባውን ቃል ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሟል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር እንዲህ ብሎ ተጽፏል፤ “ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።’
ሕግ ከሥጋ ባሕርይ የተነሣ ደክሞ ሊፈጽም ያልቻለውን፣ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኀጢአተኛ ሰው አምሳል፣ የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆን በመላክ ፈጸመው፤ በዚህም ኀጢአትን በሥጋ ኰነነ፤
አባቶችም የእነርሱ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የትውልድ ሐረጉ የሚቈጠረው ከእነርሱ ነው፤ እርሱም፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘላለም የተመሰገነ አምላክ ነው! አሜን።
እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ።
የእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ምስጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ እርሱ በሥጋ ተገለጠ፤ በመንፈስ ጸደቀ፤ በመላእክት ታየ፤ በአሕዛብ ዘንድ ተሰበከ፤ በዓለም ባሉት ታመነ፤ በክብር ዐረገ።
እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል። የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።
እግዚአብሔር፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤” ወይስ ደግሞ፣ “እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው?
እንዲሁም ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የመሆንን ክብር ለራሱ አልወሰደም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” አለው።
እግዚአብሔር ፍቅሩን በመካከላችን የገለጠው እንዲህ ነው፤ እኛ በርሱ አማካይነት በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ።
ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋል። እንዲህ ያለ ማንኛውም ሰው አታላይና የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።
ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋራ ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋራ ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል።