ዘኍል 10:10 - መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ደግሞ በደስታችሁ ቀን፥ በበዓላታችሁም ዘመን፥ በወርም መባቻ፥ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በደኅንነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት ለመታሰቢያ ይሆኑላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንዲሁም በደስታችሁ ቀናት ማለት በተደነገጉት በዓሎቻችሁና የወር መባቻ በዓል ስታከብሩ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በኅብረት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቱን ንፉ፤ እነዚህም በአምላካችሁ ፊት መታሰቢያ ይሆኑላችኋል። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እንዲሁም በደስታችሁ ቀን፥ በተወሰኑላችሁም የበዓላታችሁ ጊዜያት፥ በወራቱም መባቻዎቻችሁ፥ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በአንድነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት እንድትታወሱ ይሆኑላችኋል፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንዲሁም በደስታ በዓሎቻችሁ፥ ማለት በወር መጀመሪያና በሌሎችም የተወሰኑ በዓሎቻችሁ፥ በሚቃጠል መሥዋዕትና በአንድነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶችን ትነፋላችሁ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ስለ እናንተ አስታዋሾች ይሆናሉ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ደግሞ በደስታችሁ ቀን፥ በበዓላታችሁም ዘመን፥ በወርም መባቻ፥ በሚቃጠልም መሥዋዕታችሁና በደኅንነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶችን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት ለመታሰቢያ ይሆኑላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።” |
ካህናቱም ሰበኒያ፥ ኢዮሣፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስና አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ዖቤድኤዶምና ይሒያም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ።
እንዲሁ እስራኤል ሁሉ “ሆ!” እያሉ፥ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽል መሰንቆና በገና እየመቱ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ።
ከእነርሱም ጋር ካህናቱ ከፍ አድርገው ለማሰማት መለከትና ጸናጽል ለእግዚአብሔርም መዝሙራት የዜማ ዕቃ ይዘው ነበር፤ የኤዶታምም ልጆች በረኞች ነበሩ።
ካህናቱም በየሥርዓታቸው፥ ሌዋውያኑም ደግሞ “ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤” የሚለውን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ፥ ንጉሡ ዳዊት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሠራውን የእግዚአብሔርን የዜማ ዕቃ ይዘው ቆመው ነበር፤ ካህናቱም በፊታቸው መለከት ይነፉ ነበር፤ እስራኤልም ሁሉ ቆመው ነበር።
አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ በመሠረቱ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው፥ መለከቱን ይዘው፥ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዓት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ።
አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም መታሰቢያ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ በደረት ኪስ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም።
የማስተስረያውንም ገንዘብ ከእስራኤል ልጆች ወስደህ ለመገናኛው ድንኳን ማገልገያ ታደርገዋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ለነፍሳችሁ ቤዛ እንዲሆን ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ይሁን።
በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ታላቅ መለከት ይነፋል፥ በአሦርም የጠፉ፥ በግብጽ ምድርም የተሳደዱ ይመጣሉ፥ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ።
ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ።
በሚገፋችሁም ጠላት ላይ በምድራችሁ ወደ ሰልፍ ስትወጡ ከፍ ባለ ድምፅ መለከቶቹን ንፉ፤ በእግዚአብሔርም በአምላካችሁ ፊት ትታሰባላችሁ፥ ከጠላቶቻችሁም ትድናላችሁ።
በወሩም መባቻ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውርም የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ፦ “ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው?” አለ። መልአኩም አለው፦ “ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ።
እናንተ፦ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለተቋረጠ ነው፥ ዮርዳኖስን በተሻገረ ጊዜ የዮርዳኖስ ውኃ ተቋረጠ፥ እነዚህም ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘላለም መታሰቢያ ይሆናሉ ትሉአቸዋላችሁ።
ዳዊትም ዮናታንን አለው፦ እነሆ፥ ነገ መባቻ ነው፥ በንጉሥም አጠገብ ለምሳ አልቀመጥም፥ እስከ ሦስተኛው ቀን ማታ ድረስ በውጭ በሜዳ እንድሸሸግ አሰናብተኝ።