2 ሳሙኤል 13:23 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም ድንበር አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር ከተማ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ በዚህ ጊዜ የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ በዚያ እንዲገኙለት ጋበዛቸው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በበዓለ ሐጾር ከተማ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ ከዚያም የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ በዚያ እንዲገኙለት አቤሴሎም ጋበዛቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም ከተማ አጠገብ በዓለ ሐጾር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ ስለዚህም የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ ለግብዣ ወደዚያ ጠራ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ከሁለት ዓመትም በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር በጎቹን በሚያሸልትበት ጊዜ አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ጠራ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ከሁለት ዓመትም በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር በጎቹን አሸለተ፥ አቤሴሎምም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ጠራ። |
አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ሄዶ፣ “እነሆ፤ ባሪያህ በጎቹን እየሸለተ ነው፤ ታዲያ ንጉሡና ሹማምቱ ፈቃዳቸው ሆኖ እባክህ ይገኙልኝ?” ሲል ጠየቀው።
እርሱ በሬዎችን፣ ኰርማዎችንና በጎችን በብዛት ሠውቷል፤ የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ ካህኑን አብያታርንና የሰራዊቱን አዛዥ ኢዮአብን ጠርቷል፤ አገልጋይህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም።
በዛሬው ቀን ታች ወርዶ ብዙ በሬዎች፣ ኰርማዎችና በጎች ሠውቷል፤ የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ የሰራዊቱን አዛዦችና ካህኑን አብያታርንም ጠርቷል። እነሆ፤ አሁን፣ ‘አዶንያስ ለዘላለም ይኑር’ እያሉ ከርሱ ጋራ በመብላትና በመጠጣት ላይ ናቸው።
ከዚያም አዶንያስ በዓይንሮጌል አቅራቢያ ባለው የዞሔልት ድንጋይ አጠገብ በጎችን፣ በሬዎችንና የሠቡ ጥጆችን ሠዋ፤ ወንድሞቹን ሁሉ፣ የንጉሡን ልጆች እንዲሁም የቤተ መንግሥቱ ሹማምት የነበሩትን የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጠራ፤
እንዲሁም በየኰረብታው ግርጌና በየሜዳው ላይ ብዙ የቀንድ ከብት ስለ ነበረው፣ በምድረ በዳ የግንብ ማማዎች ሠራ፤ ብዙ የውሃ ጕድጓዶችም ቈፈረ። ግብርና ይወድድ ስለ ነበረም በኰረብታዎችና ለም በሆኑ መሬቶች ላይ ዕርሻ የሚያርሱና ወይን የሚተክሉ ሠራተኞች ነበሩት።
በማዖን ምድር በቀርሜሎስ ንብረት ያለው አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ፤ እርሱም አንድ ሺሕ ፍየሎችና በቀርሜሎስ የሚሸልታቸው ሦስት ሺሕ በጎች ነበሩት።
አቢግያም ወደ ናባል በተመለሰች ጊዜ፣ እነሆ፤ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ትልቅ ግብዣ አድርጎ አገኘችው፤ ክፉኛም ሰክሮ ልቡ በደስታ ተሞልቶ ነበር። ስለዚህ እስኪነጋ ድረስ ምንም አልነገረችውም።
“ ‘በዚህ ጊዜ በጎች እንደምትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህ ከእኛ ጋራ በነበሩበት ጊዜ፣ ያደረስንባቸው ጕዳት የለም፤ ቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፣ የጠፋባቸው አንዳች ነገር አልነበረም።