ከብዙ ተግሣጽ በኋላ ዐንገቱን የሚያደነድን ሰው፣ በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም።
በዚህ ጊዜ ከገለዓድ ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን፣ “በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ዝናብ ወይም ጠል አይኖርም” አለው።
ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ እስራኤልን አላወክሁም። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተዋችሁ፣ እነ በኣልንም ተከተላችሁ።
ነቢዩም ንጉሡን አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ ፈጽሞ ይገደል ያልሁትን ሰው ለቅቀኸዋልና በገመዱ ትገባለህ፤ በሕዝቡም ፈንታ ያንተ ሕዝብ በገመዱ ይገባል።’ ”
ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።
እርሱም በመናገር ላይ ሳለ፣ ንጉሡ፣ “ለመሆኑ አንተን የንጉሥ አማካሪ አድርገን ሾመንሃልን? ዝም አትልም እንዴ! መሞት ትፈልጋለህ?” አለው። ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም፣ “ይህን አድርገሃልና ምክሬንም አልሰማህምና፤ አምላክ ሊያጠፋህ እንደ ወሰነ ዐውቃለሁ” አለ።
እግዚአብሔር ለምናሴና ለሕዝቡ ተናገረ፤ እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም።
እንደዚሁም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ዐንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ እንጂ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም።
“ወደ ሕግህ እንዲመለሱ አስጠነቀቅሃቸው፤ እነርሱ ግን እብሪተኞች ሆኑ። ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም፤ ‘አንድ ሰው ቢፈጽማቸው በሕይወት የሚኖርባቸውን’ ሥርዐቶችህን ተላለፉ። እንቢተኞች ሆነው ጀርባቸውን አዞሩብህ፤ ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ መስማትም አልፈለጉም።
ጥበቡ ጥልቅ፣ ኀይሉም ታላቅ ነውና፤ እርሱን ተቃውሞ ያለ አንዳች ጕዳት የሄደ ማን ነው?
ፈርዖን ያጣሩ ዘንድ ሰዎች ልኮ ከእስራኤላውያኑ እንስሳት አንድም እንኳ አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ልቡ እንደ ደነደነ ስለ ነበር፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።
እግዚአብሔርን ዘወትር የሚፈራ ሰው ብፁዕ ነው፤ ልቡን የሚያደነድን ግን መከራ ላይ ይወድቃል።
አካሄዱ ነቀፋ የሌለበት ሰው ክፉ አያገኘውም፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ድንገት ይወድቃል።
ክፉዎች ሥልጣን በሚይዙ ጊዜ ሕዝብ ይሸሸጋል፤ ክፉዎች በሚጠፉበት ጊዜ ግን ጻድቃን ይበዛሉ።
ስለዚህ በቅጽበት መዓት ይወርድበታል፤ በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም።
እንግዲህ ፌዛችሁን አቁሙ፤ አለዚያ እስራታችሁ ይጸናባችኋል፤ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ መላውን ምድር ለማጥፋት ያወጀውን ዐዋጅ ሰምቻለሁ።
የቱን ያህል እልኸኛ እንደ ነበርህ ዐውቃለሁና፤ የዐንገትህ ጅማት ብረት፣ ግንባርህም ናስ ነበር።
ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ተጸየፈቻትን? ፈውስ እስከማይገኝልን ድረስ፣ ለምን ክፉኛ መታኸን? ሰላምን ተስፋ አደረግን፤ ሆኖም በጎ ነገር አላገኘንም፤ የፈውስን ጊዜ ተጠባበቅን፤ ነገር ግን ሽብር ብቻ ሆነ።
እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም ዐንገታቸውን አደነደኑ።
እርሱንና ልጆቹን መኳንንቱንም ስለ ክፋታቸው እቀጣለሁ፤ አልሰሙኝምና አመጣባቸዋለሁ ያልሁትን ጥፋት ሁሉ በእነርሱና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት፣ በይሁዳም ሕዝብ ላይ አመጣለሁ።’ ”
ባለዕዳ ያደረግሃቸው ድንገት አይነሡብህምን? ነቅተውስ አያስደነግጡህምን? በእጃቸውም ትወድቃለህ።
“ስለ ሁላችሁ መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኋቸውን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን፣ ‘እንጀራዬን የሚበላ ተረከዙን አነሣብኝ’ የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው።
ኢየሱስም፣ “ይህን ቍራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አለው፤ ከዚያም ቍራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው።
ይህ ሰው ስለ ክፉ ሥራው በተከፈለው ዋጋ መሬት ገዛ፤ በዚያም በግንባሩ ተደፍቶ ሰውነቱ እመካከሉ ላይ ፈነዳ፤ ሆድ ዕቃውም ተዘረገፈ።
ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ትቶት በሄደው በዚህ አገልግሎትና በሐዋርያዊነት ቦታ ላይ ሹመው።”
ሰዎች፣ “ሰላምና ደኅንነት ነው” ሲሉ፣ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት እንዲሁ ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም።
አንድ ሰው ሌላውን ቢበድል፣ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ይፈርዳል፤ ነገር ግን ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል፣ ማን ይማልድለታል?” ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ፣ ልጆቹ የአባታቸውን ተግሣጽ አልሰሙም።
“ ‘በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚደርሰው ላንተ ምልክት ይሆንሃል፣ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ።