“አንተ ትዕቢተኛ፤ እነሆ፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ “የምትቀጣበት ጊዜ፣ ቀንህ ደርሷልና።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እብሪተኛውንና ትዕቢተኛውን ሁሉ፣ የተኵራራውን በሙሉ የሚያዋርድበት ቀን አለው።
ከሸለቆው በላይ፣ በድንጋያማው ዐምባ ላይ የምትኖሪ ሆይ፤ እኔ በአንቺ ላይ ወጥቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር። “ማን በእኛ ላይ ይወጣል? ማንስ ወደ መኖሪያችን ደፍሮ ይገባል?” የምትሉ ሆይ፤
“ስለ ሞዓብ ትዕቢት፣ ስለ እብሪቱና ስለ ኵራቱ፣ ስለ ትምክሕቱና ስለ መጓደዱ፣ ስለ ልቡም ማበጥ ሰምተናል።
አንተ በዐለት ንቃቃት ውስጥ የምትኖር፣ የተራራውንም ከፍታ የያዝህ ሆይ፤ የምትነዛው ሽብር፣ የልብህም ኵራት አታልሎሃል፤ መኖሪያህን እስከ ንስር ከፍታ ቦታ ብትሠራም፣ ከዚያ ወደ ታች አወርድሃለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር።
“ቀስት የሚገትሩትን፣ ቀስተኞችን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩ፤ አንድም ሰው እንዳያመልጥ፣ ዙሪያውን ሁሉ መሽጉ፤ የእስራኤልን ቅዱስ፣ እግዚአብሔርን አቃልላለችና፣ እንደ ሥራዋ መጠን መልሱላት፤ በሌሎች ላይ እንዳደረገችውም አድርጉባት።
ትዕቢተኛው ይሰናከላል፤ ይወድቃልም፤ የሚያነሣውም የለም፤ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ የሚበላ እሳት፣ በከተሞቹ ውስጥ አስነሣለሁ።”
“አንቺ ምድርን ሁሉ ያጠፋሽ፣ አጥፊ ተራራ ሆይ፤ እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፣” ይላል እግዚአብሔር፤ “እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ ከገመገም ቍልቍል አንከባልልሻለሁ፤ የተቃጠለም ተራራ አደርግሻለሁ።
እንዲህም ብለህ ተናገረው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። “ ‘በወንዞችህ መካከል የምትተኛ አንተ ታላቅ አውሬ፣ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ። “የአባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ ለራሴም ሠርቼዋለሁ” ትላለህ።
እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የሜሼኽና የቶቤል ዋና አለቃ ጎግ ሆይ፤ ተነሥቼብሃለሁ።
“አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ በጎግ ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የሜሼኽና የቶቤል ዋና አለቃ ጎግ ሆይ፤ ተነሥቼብሃለሁ፤
“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ፤ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በአሕዛብም ፊት ፍርድ አመጣብሻለሁ።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በእናንተ ላይ ተነሥቼባችኋለሁ፤ ሠረገሎቻችሁን አቃጥዬ አጨሳለሁ፤ ደቦል አንበሶቻችሁን ሰይፍ ይበላል፤ የምትበሉትን በምድር ላይ አልተውላችሁም፤ የመልእክተኞቻችሁም ድምፅ፣ ከእንግዲህ ወዲያ አይሰማም።”
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እኔ በጠላትነት ተነሥቼብሻለሁ፤ ቀሚስሽን እስከ ፊትሽ እገልበዋለሁ፤ ዕርቃንሽን ለአሕዛብ፣ ኀፍረትሽንም ለነገሥታት አሳያለሁ።
ነገር ግን ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል፤ መጽሐፍም፣ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ያለው ስለዚህ ነው።
ጕልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”
ስለዚህ መቅሠፍቶቿ በአንድ ቀን ይመጡባታል፤ ሞት፣ ሐዘንና ራብ ይሆኑባታል፤ የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ስለ ሆነ፣ በእሳት ትቃጠላለች።