“ለምን በእኔ ታማርራላችሁ? ያመፃችሁብኝ እናንተ ሁላችሁ ናችሁ፤” ይላል እግዚአብሔር።
“ ‘አልረከስሁም፣ በኣሊምን አልተከተልሁም’ እንዴት ትያለሽ? በሸለቆ ውስጥ ምን እንዳደረግሽ እስኪ አስቢ፣ ምንስ እንደ ፈጸምሽ ተገንዘቢ፤ እንደምትፋንን ፈጣን ግመል ሆነሻል፤
‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤ በርግጥ ቍጣው ከእኔ ርቋል’ ትያለሽ። እኔ ግን እፈርድብሻለሁ፤ ‘ኀጢአት አልሠራሁም’ ብለሻልና።
“እስኪ ቀና ብለሽ ጭር ያሉትን ኰረብቶች ተመልከቺ፣ በርኩሰት ያልተጋደምሽበት ቦታ ይገኛልን? በበረሓ እንደ ተቀመጠ ዘላን ዐረብ፣ በየመንገዱ ዳር ተቀምጠሽ ወዳጆችሽን ጠበቅሽ። በዝሙትሽና በክፋትሽ፣ ምድሪቱን አረከስሽ።
“በኢየሩሳሌም መንገዶች እስኪ ውጡ፤ ወደ ላይ ወደ ታችም ውረዱ፤ ዙሪያውን ተመልከቱ ቃኙ፤ በአደባባይዋም ፈልጉ፤ እውነትን የሚሻና በቅንነት የሚሄድ፣ አንድ ሰው እንኳ ብታገኙ፣ እኔ ይህችን ከተማ እምራታለሁ።
“ከትንሹ እስከ ትልቁ ሰው፣ ሁሉም ለጥቅም የሚስገበገቡ ናቸው፤ ነቢያቱም ካህናቱም ሳይቀሩ፣ ሁሉም ያጭበረብራሉ።
መላው እስራኤል አንተን ባለመታዘዝ ሕግህን ተላልፏል፤ ዘወርም ብሏል። “በአንተ ላይ ኀጢአትን ስለ ሠራን፣ በእግዚአብሔር አገልጋይ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላና ርግማን ፈሰሰብን።
እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደ ሆነ፣ እናውቃለን፤