ታዲያ፣ ልታመልካቸው ያበጀሃቸው አማልክት ወዴት ናቸው? በመከራህ ጊዜ ሊያድኑህ የሚችሉ ከሆነ፣ ይሁዳ ሆይ፤ እስኪ ይምጡና ያድኑህ፤ የከተሞችህን ቍጥር ያህል፣ የአማልክትህም ብዛት እንዲሁ ነውና።
ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ፤ “ከአንተ ጋራ ምን የሚያገናኘን ጕዳይ አለና መጣህ፤ አሁን የአባትህና የእናትህ ነቢያት ወዳሉበት ሂድ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፣ “ይህማ አይሆንም፤ በሞዓብ እጅ አሳልፎ ሊሰጠን እኛን ሦስት ነገሥታት አንድ ላይ የጠራን እግዚአብሔር ነው” አለ።
“በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ቅረቡም፤ እናንተ ከአሕዛብ የኰበለላችሁ፣ ኑ። የዕንጨት ጣዖት የሚሸከሙ፣ ማዳን ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ፣ ዕውቀት የላቸውም።
እነርሱም በአንድ ላይ ዝቅ ይላሉ፤ ያጐነብሳሉ፤ ጭነቱን ለማዳን አይችሉም፤ ራሳቸውም በምርኮ ይወሰዳሉ።
አንሥተው በትከሻቸው ይሸከሙታል፤ እቦታው ያደርጉታል፤ በዚያም ይቆማል፤ ከዚያም ቦታ አይንቀሳቀስም፤ ማንም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይመልስም፤ ከጭንቀቱም አያድነውም።
ለርዳታ በምትጮኺበት ጊዜ፣ የሰበሰብሻቸው ጣዖቶች እስኪ ያድኑሽ! ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ሽውሽውታም ይበትናቸዋል። እኔን መጠጊያው ያደረገ ሰው ግን፣ ምድሪቱን ይወርሳል፤ የተቀደሰ ተራራዬንም ገንዘቡ ያደርገዋል።”
እኔን በመተው ክፋት ስለ ሠሩ፣ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣ እጆቻቸው የሠሯቸውን ስላመለኩ፣ በሕዝቤ ላይ ፍርድን ዐውጄአለሁ።
የይሁዳ ከተሞችና የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ወደሚያጥኑላቸው አማልክት ሄደው ይጮኻሉ፤ እነርሱ ግን በመከራቸው ጊዜ ከቶ ሊረዷቸው አይችሉም።
ይሁዳ ሆይ፤ የአማልክትህ ቍጥር የከተሞችህን ብዛት ያህል ነው፤ አሳፋሪ ለሆነው ጣዖት፣ ለበኣል ማጠኛ የሠራችኋቸው መሠዊያዎቻችሁ ብዛት የኢየሩሳሌምን መንገዶች ያህል ነው።’
ወዮ ለዚያ ቀን! እንደዚያም ያለ አይኖርም፤ ለያዕቆብ የመከራ ጊዜ ነው፤ ነገር ግን ይተርፋል።
ለመሆኑ፣ ‘የባቢሎን ንጉሥ እናንተንም ይህችንም ምድር አይወጋም’ ብለው ትንቢት ይናገሩ የነበሩት ነቢያታችሁ ወዴት ናቸው?
እስራኤል የተንዠረገገ ወይን ነበር፤ ብዙ ፍሬም አፈራ፤ ፍሬው በበዛ መጠን፣ ብዙ መሠዊያዎችን ሠራ፤ ምድሩ በበለጸገ መጠን፣ የጣዖታት ማምለኪያ ዐምዶችን አስጌጠ።
“የሰው እጅ የቀረጸው ጣዖት፣ ሐሰትንም የሚናገር ምስል ምን ፋይዳ አለው? ሠሪው በገዛ እጁ ሥራ ይታመናልና፣ መናገር የማይችሉ ጣዖታትን ይሠራልና።
ዕንጨቱን፣ ‘ንቃ!’ ሕይወት የሌለውንም ድንጋይ፣ ‘ተነሣ!’ ለሚል ወዮለት! በውኑ ማስተማር ይችላልን? እነሆ፤ በወርቅና በብር ተለብጧል፤ እስትንፋስም የለውም።”
እንዲህም ይላል፤ “መጠጊያ ዐለት የሆኗቸው፣ እነዚያ አማልክታቸው የት አሉ?
ሂዱና ወደ መረጣችኋቸው አማልክት ጩኹ፤ መከራ በሚያገኛችሁ ጊዜ እስኪ ያድኗችሁ።”