ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ፤ ለክብሬ መግለጫ ይሆኑ ዘንድ፣ የእጆቼ ሥራ፣ እኔ የተከልኋቸው ቍጥቋጦች ናቸው።
የራሳቸውም መኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው፣ ከእንግዲህ በኋላም እንዳይናወጡ ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ ስፍራ እሰጣቸዋለሁ። ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ክፉዎች ከእንግዲህ አይጨቍኗቸውም፤
ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።
እግዚአብሔር የንጹሓንን የሕይወት ዘመን ያውቃል፤ ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል።
እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤ እርሱ የሚረግማቸው ግን ይጠፋሉ።
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።
በእግዚአብሔር ቤት ተተክለዋል፤ በአምላካችንም አደባባይ ይንሰራፋሉ።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርም፣ “ሕዝቤ ግብጽ፣ የእጄ ሥራ አሦር፣ ርስቴም እስራኤል የተባረኩ ይሁኑ” ብሎ ይባርካቸዋል።
“ለጻድቁ ክብር ይሁን” የሚል ዝማሬ፣ ከምድር ዳርቻ ሰማን። እኔ ግን፣ “ከሳሁ፤ መነመንሁ፤ ወዮልኝ! ከዳተኞች አሳልፈው ሰጡ፤ ከዳተኞች በክሕደታቸው አሳልፈው ሰጡ” አልሁ።
በእምነቱ የጸና ጻድቅ የሆነ ሕዝብ ይገባ ዘንድ፣ በሮቿን ክፈቱ።
በመካከላቸው የእጄ ሥራ የሆኑ፣ ልጆቻቸውን ሲያዩ፣ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብን ቅዱስ ቅድስና ያውቃሉ፤ በእስራኤልም አምላክ ፊት በፍርሀት ይቆማሉ።
ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ ምስጋናዬን ያውጅ ዘንድ ይህን አደርጋለሁ።
በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ።”
ሰማያት ሆይ፤ እግዚአብሔር ይህን አድርጓልና ዘምሩ፤ የምድር ጥልቆች ሆይ፤ በደስታ ጩኹ። እናንተ ተራሮች፣ እናንተ ደኖችና ዛፎቻችሁ ሁሉ እልል በሉ፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቷል፣ በእስራኤልም ክብሩን ገልጧልና።
“የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም የሆነ እግዚአብሔር፣ ስለሚመጡ ነገሮች እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ልጆቼ ትጠይቁኛላችሁን? ስለ እጆቼስ ሥራ ታዝዙኛላችሁን?
ስለ እኔም ሲናገሩ፣ ‘ጽድቅና ኀይል፣ በእግዚአብሔር ብቻ ነው’ ይላሉ።” በርሱ ላይ በቍጣ የተነሡ ሁሉ፣ ወደ እርሱ መጥተው ያፍራሉ።
ነገር ግን የእስራኤል ዘር ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፤ ሞገስንም ያገኛሉ።
“እናንተ ሰማያት፣ ጽድቅን ከላይ አዝንቡ፤ ደመናትም ወደ ታች አንጠብጥቡ፤ ምድር ትከፈት፤ ድነት ይብቀል፤ ጽድቅም ዐብሮት ይደግ፤ እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ።
እርሱም፣ “እስራኤል፤ አንተ ባሪያዬ ነህ፤ በአንተ ክብሬን እገልጣለሁ” አለኝ።
ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፣ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፤ በጠራሁት ጊዜ አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ ባረክሁት፤ አበዛሁትም።
ጽዮን ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤ ኀይልን ልበሺ፤ ቅድስቲቱ ከተማ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ! የክብር ልብስሽን ልበሺ፤ ያልተገረዘ የረከሰም ከእንግዲህ ወደ አንቺ አይገባም።
በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፤ ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው፤” ይላል እግዚአብሔር።
ለርዳታ በምትጮኺበት ጊዜ፣ የሰበሰብሻቸው ጣዖቶች እስኪ ያድኑሽ! ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ሽውሽውታም ይበትናቸዋል። እኔን መጠጊያው ያደረገ ሰው ግን፣ ምድሪቱን ይወርሳል፤ የተቀደሰ ተራራዬንም ገንዘቡ ያደርገዋል።”
ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣ የተክል ቦታ ችግኝ እንደሚያፈላ፣ ጌታ እግዚአብሔርም በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣ ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል።
በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
ሕዝቤ በኀፍረታቸው ፈንታ፣ ዕጥፍ ይቀበላሉ፤ በውርደታቸው ፈንታ፣ በርስታቸው ደስ ይላቸዋል፤ የምድራቸውንም ዕጥፍ ርስት ይወርሳሉ፤ ዘላለማዊ ደስታም የእነርሱ ይሆናል።
ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤ ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤ ነገር ግን፣ “ደስታዬ በርሷ” ትባያለሽ፤ ምድርሽም፣ “ባለባል” ትባላለች፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ ምድርሽም ባለባል ትሆናለች።
ይህም ሆኖ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ሸክላዎች፣ አንተም ሸክላ ሠሪ ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን፤
ከያዕቆብ ዘር የሆኑትን፣ ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሱትን አመጣለሁ። የተመረጠው ሕዝቤ ይወርሳቸዋል፤ ባሪያዎቼም በዚያ ይኖራሉ።
ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።
ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ።’
“ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከአሕዛብ መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባቸው አገሮች እመልሳችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እንደ ገና እሰጣችኋለሁ።’
ከእንግዲህ በምድሪቱ ላይ የራብ ተጠቂ እንዳይሆኑ፣ የአሕዛብንም ስድብ እንዳይሸከሙ ፍሬ በመስጠት የታወቀውን መሬት እሰጣቸዋለሁ።
አባቶቻችሁ በኖሩበት፣ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠሁት ምድር ይኖራሉ። በዚያም እነርሱ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘላለም ይኖራሉ፤ ባሪያዬ ዳዊትም ለዘላለም ንጉሣቸው ይሆናል።
እዚያም በደረስሁ ጊዜ፣ በወንዙ ግራና ቀኝ ብዙ ዛፍ አየሁ።
እስራኤልን በገዛ ምድራቸው እተክላቸዋለሁ፤ ከሰጠኋቸውም ምድር፣ ዳግመኛ አይነቀሉም፤” ይላል አምላክህ እግዚአብሔር።
ነገር ግን በጽዮን ተራራ ነጻ መውጣት ይሆናል፤ የያዕቆብ ቤትም እርሷ የተቀደሰች ትሆናለች፤ ርስታቸውን ይወርሳሉ።
የእስራኤል ቅሬታዎች ኀጢአት አይሠሩም፤ ሐሰትም አይናገሩም፤ በአንደበታቸውም ተንኰል አይገኝም። ይበላሉ፤ ይተኛሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም።”
እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል።
የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።
እርሱም በእኔ ያለውን፣ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቈርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ግን የበለጠ እንዲያፈራ ይገርዘዋል።
ይኸውም በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው።
ይኸውም፣ በሚወድደው በርሱ በኩል በነጻ የተሰጠን ክቡር የሆነው ጸጋው እንዲመሰገን ነው።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
ይኸውም በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ በቸርነቱ የገለጠልንን ወደር የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ነው።
የሚቀጡትም በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብርና በሚያምኑበትም ሁሉ ሊገረም በሚመጣበት በዚያ ቀን ይሆናል፤ እናንተም ከሚያምኑት መካከል ናችሁ፤ ምስክርነታችንን ተቀብላችኋልና።
እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን።
በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፣ ርኩሰትን የሚያደርግና ውሸትን የሚናገር ሁሉ አይገባባትም።
ድል የሚነሣ ይህን ሁሉ ይወርሳል፤ እኔም አምላክ እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል።
ለአምላካችንም መንግሥትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤ እነርሱም በምድር ላይ ይነግሣሉ።”