ፀሓይሽ ከእንግዲህ አትጠልቅም፤ ጨረቃሽም ብርሃን መስጠቷን አታቋርጥም፤ እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናል፤ የሐዘንሽም ቀን ያከትማል።
እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኅኔ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር ለሕይወቴ ዐምባዋ ነው፤ ማንን እፈራለሁ?
እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ያለ ነቀፋ የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም፣ በሽማግሌዎቹም ፊት በክብሩ ይነግሣል፤ ጨረቃ ትሸማቀቃለች፤ ፀሓይም ታፍራለች።
ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤ የሕዝቡንም ውርደት ከምድር ሁሉ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሯልና።
በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅሱም። ለርዳታ ወደ እርሱ ስትጮኹ እንዴት ምሕረት አያደርግላችሁ! ጩኸትህን እንደ ሰማም ፈጥኖ ይመልስልሃል።
እግዚአብሔር የሕዝቡን ስብራት ሲጠግን፣ ያቈሰለውንም ሲፈውስ፣ ጨረቃ እንደ ፀሓይ ታበራለች፤ የፀሓይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት ዕጥፍ ይደምቃል።
እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘላለማዊ ደስታን ይጐናጸፋሉ፤ ደስታና ሐሤት ይቀድማሉ፤ ሐዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።
“ብርሃንሽ መጥቷልና ተነሺ አብሪ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻል።
በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
በኢየሩሳሌም እደሰታለሁ፤ በሕዝቤ ሐሤት አደርጋለሁ፤ የልቅሶና የጩኸት ድምፅ፣ ከእንግዲህ በዚያ አይሰማም።
መጥተውም በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በእግዚአብሔርም ልግስና፣ በእህሉ፣ በወይን ጭማቂውና በዘይቱ፣ በፍየልና በበግ ጠቦት፣ በወይፈንና በጊደር ደስ ይሰኛሉ፤ ውሃ እንደማይቋረጥባት የአትክልት ስፍራ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህም አያዝኑም።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞው አድስ፤
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን፣ ፀሓይ በቀትር እንድትጠልቅ አደርጋለሁ፤ ምድርንም ደማቅ ብርሃን ሳለ በቀን አጨልማታለሁ።
ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀን በእግዚአብሔር የታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል።
ስሜን ለምትፈሩ ለእናንተ ግን የጽድቅ ፀሓይ በክንፎቿ ፈውስ ይዛ ትወጣለች፤ እናንተም እንደ ሠባ እንቦሳ እየቦረቃችሁ ትወጣላችሁ።
የእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ስለሚሰጣትና በጉም መብራቷ ስለ ሆነ፣ ከተማዋ ፀሓይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም።
እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፏልና።”