በሮችሽ ምን ጊዜም የተከፈቱ ይሆናሉ፤ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቶ አይዘጉም፤ ይህም ሰዎች የመንግሥታትን ብልጽግና ወደ አንቺ እንዲያመጡ፣ ነገሥታታቸውም በድል ወደ አንቺ እንዲገቡ ነው።
በሰንበት ዋዜማ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ የምሽቱ ጥላ ማረፍ ሲጀምር በሮቹ እንዲዘጉና፣ ሰንበት እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ፤ በሰንበት ቀን ጭነት እንዳይገባም ከራሴ ሰዎች አንዳንዶቹን በየበሩ ላይ አቆምሁ።
ነገሥታታቸውን በሰንሰለት፣ መኳንንታቸውንም በእግር ብረት ያስራሉ፤
በዚያ ቀን እግዚአብሔር፣ በላይ በሰማያት ያሉትን ኀይሎች፣ በታችም በምድር ያሉትን ነገሥታት ይቀጣቸዋል።
በእምነቱ የጸና ጻድቅ የሆነ ሕዝብ ይገባ ዘንድ፣ በሮቿን ክፈቱ።
ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ፣ እቴጌዎቻቸው ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዱልሻል፤ የእግርሽን ትቢያ ይልሳሉ፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፤ እኔን ተስፋ የሚያደርጉም አያፍሩም።”
ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ። የሚቃጠል መሥዋዕታቸውንና ሌሎች መሥዋዕቶቻቸውን፣ በመሠዊያዬ ቢሠዉ እቀበላቸዋለሁ፤ ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራልና።”
ከእንግዲህ በምድርሽ ሁከት፣ በጠረፎችሽም ጥፋትና መፈራረስ አይሰማም፤ ነገር ግን ቅጥሮችሽን ድነት፣ በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያቸዋለሽ።
ከዚያም ታያለሽ፤ ታብረቀርቂአለሽ፤ ልብሽ ይዘልላል፤ በደስታም ይሞላል። በባሕሮች ያለው ሀብት ወደ አንቺ ይመጣል፤ የነገሥታትም ብልጽግና የአንቺ ይሆናል።
እናንተም የእግዚአብሔር ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ የአምላካችን ባሮች ትባላላችሁ፤ የመንግሥታትን ሀብት ትመገባላችሁ፤ በብልጽግናቸውም ትኰራላችሁ።
ዕለፉ፤ በበሮቹ በኩል ዕለፉ፤ ለሕዝቡ መንገድ አዘጋጁ፤ አስተካክሉ፤ ጐዳናውን አስተካክሉ! ድንጋዩን አስወግዱ፤ ለመንግሥታትም ምልክት አሳዩ።