እነሆ፤ ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤ አንዳንዶች ከሰሜን ሌሎች ከምዕራብ፣ የቀሩት ደግሞ ከሲኒም ይመጣሉ።”
የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስታውሳሉ፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳሉ፤ የሕዝቦች ነገዶች ሁሉ፣ በፊቱ ይሰግዳሉ።
ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ ዝናው ፀሓይ የምትኖረውን ዘመን ያህል ይዝለቅ። ሕዝቦች ሁሉ በርሱ ይባረኩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ቡሩክ ነህ ይበለው።
ለመንግሥታት ምልክትን ያቆማል፤ ከእስራኤልም የተሰደዱትን መልሶ ያመጣቸዋል፤ የተበተኑትን የይሁዳ ሕዝብ፣ ከአራቱ የምድር ማእዘን ይሰበስባል።
“እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፣ እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና፤ ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ።
እናንተ ደሴቶች ስሙኝ፤ እናንተ በሩቅ ያላችሁ ሕዝቦች ይህን አድምጡ፤ በእናቴ ማሕፀን ሳለሁ እግዚአብሔር ጠራኝ፤ ከመወለዴ በፊት በስም ጠራኝ።
ዐይንሽን ቀና አድርጊ፤ ዙሪያውንም ተመልከቺ፤ ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝ፤ እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤ እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊያቸዋለሽ” ይላል እግዚአብሔር።
እነሆ፤ የማታውቃቸውን መንግሥታት ትጠራለህ፤ የማያወቁህ መንግሥታት በፍጥነት ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክህ፣ የእስራኤል ቅዱስ፣ በክብሩ ከፍ ከፍ አድርጎሃል።”
በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም ይፈራሉ፤ በፀሓይ መውጫ ያሉት ለክብሩ ይገዛሉ፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ እንደ ተቋተ፣ እንደ ተከማቸም ጐርፍ ይመጣልና።
“ቀና በዪ፤ ዙሪያሽን ተመልከቺ፤ ሁሉም ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆችሽም በዕቅፍ ወደ አንቺ ይመጣሉ።
“ ‘ስለዚህ፤ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤ እስራኤል ሆይ፤ አትደንግጥ፤’ ይላል እግዚአብሔር። ‘አንተን ከሩቅ አገር፣ ዘርህንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ፤ ያዕቆብ ተመልሶ በሰላምና በርጋታ ይቀመጣል፤ የሚያስፈራውም አይኖርም።
ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ በጐዳናውም እንድንሄድ፣ መንገዱን ያስተምረናል።” ሕግ ከጽዮን፤ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።
“በዚያ ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፤ የእኔም ሕዝብ ይሆናሉ። በመካከልሽ እኖራለሁ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ አንቺ እንደ ላከኝም ታውቃላችሁ።
እነዚያ በሩቅ ያሉት መጥተው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሲሠራ ያግዛሉ፤ እናንተም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር በጥንቃቄ ብትታዘዙ ይህ ይሆናል።”
እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ በማእድ ይቀመጣሉ፤
ሰዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ መጥተው በእግዚአብሔር መንግሥት በማእድ ይቀመጣሉ።
ሰባተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም እንዲህ የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ፤ “የዓለም መንግሥት፣ የጌታችንና የርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች፤ እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”
ከዚህም በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው፣ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው ነበር።