ከዚያም ከዘብ ቤቱ የኋላ ግድግዳ ጀምሮ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ ያለውን የመግቢያ በር ለካ፤ ከአንዱ መከለያ ግድግዳ እስከ ሌላው መከለያ ግድግዳ ያለው ርቀት ሃያ ዐምስት ክንድ ነበር።
በእያንዳንዱ ዘብ ቤት ፊት ለፊት ከፍታው አንድ ክንድ የሆነ መከለያ የግንብ ዐጥር አለ፤ የዘብ ቤቶቹም ስፋት እኩል በኩል ስድስት ክንድ ነበር።
በመግቢያው በር ዙሪያ ባሉት ወጣ ወጣ ባሉት ግንቦች ሁሉ ፊት ለፊት ያለውን ቦታ ለካ፤ ስድሳ ክንድም ነበር። የተለካውም ከአደባባዩ ፊት ለፊት እስካለው መተላለፊያ በረንዳ ድረስ ነበር።
እንደ መጀመሪያው በር ሁሉ ይኸኛውም በየጐኑ ያሉት ሦስት ሦስት የዘብ ቤቶች፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉ ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው እኩል ነበር። ርዝመቱ ዐምሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ ዐምስት ክንድ ነበር።