በእያንዳንዱ ዘብ ቤት ፊት ለፊት ከፍታው አንድ ክንድ የሆነ መከለያ የግንብ ዐጥር አለ፤ የዘብ ቤቶቹም ስፋት እኩል በኩል ስድስት ክንድ ነበር።
ከዚያም የበሩን ስፋት ለካ፤ ወርዱ ዐሥር ክንድ፣ ርዝመቱም ዐሥራ ሦስት ክንድ ነበር።
ከዚያም ከዘብ ቤቱ የኋላ ግድግዳ ጀምሮ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ ያለውን የመግቢያ በር ለካ፤ ከአንዱ መከለያ ግድግዳ እስከ ሌላው መከለያ ግድግዳ ያለው ርቀት ሃያ ዐምስት ክንድ ነበር።
ክፍሎቹ እንደ መተላለፊያ በረንዳዎቹ ከግራና ከቀኝ በኩል ትንንሽ መስኮቶች አሏቸው። በዙሪያው ያሉ መስኮቶች በመግቢያው በር ፊት ለፊት የነበሩ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ክፍል ግራና ቀኝ ግድግዳ ላይ ደግሞ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾበታል።
የዘብ ቤቶቹ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው ከሌሎቹ ጋራ ተመሳሳይ ነበር። መግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳዎቹ ዙሪያቸውን መስኮቶች ነበሯቸው። ርዝመቱ ዐምሳ ክንድ ወርዱም ሃያ ዐምስት ክንድ ነበር።
በእያንዳንዱ የውስጥ መግቢያ በር መተላለፊያ በረንዳ አጠገብ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚታጠብበት በር ያለው ክፍል አለ።
የዘብ ጠባቂ ቤቶች፣ ቁመታቸው አንድ መለኪያ ዘንግ፣ ወርዳቸውም አንድ መለኪያ ዘንግ ነበር፤ በቤቶቹም መካከል ያሉት ግንቦች ውፍረት ዐምስት ክንድ ነበር። ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ባለው መተላለፊያ በረንዳ አጠገብ በውስጥ በኩል ያለው የበሩ መድረክ ወለል አንድ ዘንግ ነበር።