ሰው መናገር ከሚችለው በላይ፣ ነገሮች ሁሉ አድካሚ ናቸው፤ ዐይን ከማየት አይጠግብም፤ ጆሮም በመስማት አይሞላም።
ነፍሴ በቅቤና በሥብ እንደሚረካ ሰው ትረካለች፤ አፌም በሚያዜሙ ከንፈሮች በደስታ ያወድስሃል።
ሲኦልና የሙታን ዓለም እንደማይጠግቡ ሁሉ፣ የሰውም ዐይን አይረካም።
ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳሉ፤ ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤ ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ።
ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣ ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣ ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፤ ከፀሓይ በታች ምንም ትርፍ አልነበረም።
አምላክ፣ ደስ ለሚያሠኘው ሰው ጥበብን፣ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል። ለኀጢአተኛ ግን፣ አምላክን ደስ ለሚያሠኘው ይተውለት ዘንድ፣ ሀብትን የመሰብሰብና የማከናወን ተግባር ይሰጠዋል። ይህም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
ልጅም ሆነ ወንድም የሌለው፣ ብቸኛ ሰው አለ፤ ጥረቱ ማለቂያ የለውም፤ ዐይኑም ባለው ሀብት ገና አልረካም፤ እርሱም፣ “ለማን ብዬ ነው የምደክመው? ራሴን ከማስደሰትስ የምቈጠበው ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ፣ የጭንቅ ኑሮ ነው።
የሰው ጥረት ሁሉ ለአፉ ነው፤ ፍላጎቱ ግን ፈጽሞ አይረካም።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ብዙ ተስፋ አደረጋችሁ፤ ያገኛችሁት ግን ጥቂት ነው፤ ወደ ቤት ያስገባችሁትንም እኔ እፍ አልሁበት፤ ይህ የሆነው ለምን ይመስላችኋል? የእኔ ቤት ፈርሶ እያለ ሁላችሁም የራሳችሁን ቤት ለመሥራት ስለ ሮጣችሁ ነው፤
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ።
ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና።